ክርስቲያናዊ ሕይወት
ወጣቶች—ይሖዋ የቅርብ ጓደኛችሁ ነው?
ምን ዓይነት ባሕርይ ያለው ጓደኛ ቢኖራችሁ ደስ ይላችኋል? ጓደኛችሁ ታማኝ፣ ደግና ለጋስ ቢሆን እንደምትደሰቱ ጥያቄ የለውም። ይሖዋ እነዚህ ባሕርያት በሙሉ አሉት። (ዘፀ 34:6፤ ሥራ 14:17) ወደ እሱ ስትጸልዩ ይሰማችኋል። የእሱን እገዛ ስትፈልጉ ሊረዳችሁ ዝግጁ ነው። (መዝ 18:19, 35) እንዲሁም ስህተት ስትሠሩ ይቅር ይላችኋል። (1ዮሐ 1:9) ይሖዋ በእርግጥም ጥሩ ጓደኛ ነው!
ከይሖዋ ጋር ጓደኝነት መመሥረት የምትችሉት እንዴት ነው? ቃሉን በማንበብ ስለ እሱ ተማሩ። የልባችሁን ግልጥልጥ አድርጋችሁ ንገሩት። (መዝ 62:8፤ 142:2) እሱ ከፍ አድርጎ ለሚመለከታቸው ነገሮች ትልቅ ቦታ እንደምትሰጡ አሳዩ፤ ከእነዚህ መካከል ልጁ፣ መንግሥቱና ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሰጣቸው ተስፋዎች ይገኙበታል። ስለ እሱ ለሌሎች ተናገሩ። (ዘዳ 32:3) ከይሖዋ ጋር የቅርብ ወዳጅነት ከመሠረታችሁ እሱ ለዘላለም ጓደኛችሁ ይሆናል።—መዝ 73:25, 26, 28
ወጣቶች—“ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም” የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት፤ ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
-
ራሳችሁን ወስናችሁ ለመጠመቅ መዘጋጀት የምትችሉት እንዴት ነው?
-
በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ለይሖዋ በምታቀርቡት አገልግሎት ረገድ ሊረዷችሁ የሚችሉት እንዴት ነው?
-
አገልግሎት ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ዝምድና የሚያጠናክረው እንዴት ነው?
-
የትኞቹ የአገልግሎት መስኮች ተከፍተውላችኋል?
-
ከይሖዋ ባሕርያት መካከል የምትወዱት የትኛውን ነው?