በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ስታኒስላቭ ቴሊያትኒኮቭ፣ ሊትዌኒያ

ሰኔ 15, 2022
ሊትዌኒያ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ባስተላለፈው ብይን ሊትዌኒያ የወንድም ስታኒስላቭ ቴሊያትኒኮቭን አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የመስጠት መብት ነፍጋለች አለ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ባስተላለፈው ብይን ሊትዌኒያ የወንድም ስታኒስላቭ ቴሊያትኒኮቭን አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የመስጠት መብት ነፍጋለች አለ

ሰኔ 7, 2022 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የወንድም ስታኒስላቭ ቴሊያትኒኮቭን ክስ ከተመለከተ በኋላ በሊትዌኒያ ላይ በአንድ ድምፅ ውሳኔ አስተላልፏል፤ ወንድም ስታኒስላቭ ቴሊያትኒኮቭ በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ የይሖዋ ምሥክር ነው። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት እንደገለጸው በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 9 (የሐሳብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነፃነት) መሠረት ግለሰቦች በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆን መብት አላቸው። የሊትዌኒያ ውሳኔ ይህን ድንጋጌ የሚጥስ በመሆኑ ለስታኒስላቭ 3,000 ዩሮ (3,196 የአሜሪካ ዶላር) እንድትከፍል ተጠይቃለች።

አብዛኞቹ የአውሮፓ ምክር ቤት አባል አገራት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት መስጠት የሚቻልበትን አሠራር ተፈጻሚ አድርገዋል። ስታኒስላቭ ለውትድርና ሲመለመል ከዚህ የአውሮፓ አሠራር ጋር በሚስማማ መልኩ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ለመስጠት ጥያቄ አቀረበ። ሆኖም ሊትዌኒያ ይህን አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት አሠራር አልዘረጋችም። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በሊትዌኒያ ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ከዚህ ቀደም በቱርክ፣ በአርሜንያ እና በአዘርባጃን ላይ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች የሚያስተጋባ ነው፤ ፍርድ ቤቱ በድጋሚ አበክሮ እንደገለጸው ሁሉም የአውሮፓ ምክር ቤት አባል አገራት አማራጭ የሲቪል አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ሥርዓት መዘርጋት ያለባቸው ሲሆን ይህ አገልግሎት መቅጫ ያልሆነ፣ አድሏዊነት የሌለበትና ከውትድርና ጋር ምንም ንክኪ የሌለው ሊሆን ይገባል።

ከዚያ ወዲህ አርሜንያ ውጤታማ የሆነ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ዘርግታለች። በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ወጣት ወንዶች በምትኩ ልማታዊ በሆኑ ሕዝባዊ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ ይፈቀድላቸዋል።

ሊትዌኒያም የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቀበል አማራጭ የሲቪል አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ሥርዓት ለዜጎቿ እንደምትዘረጋ ተስፋ እናደርጋለን፤ ይህ ወንድሞቻችንን ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡንም የሚጠቅም አካሄድ ነው። እስከዚያው ግን ይሖዋ በሊትዌኒያ ያሉ ወንድሞቻችንን እንደሚመራቸውና የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው እንተማመናለን።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:25