ነሐሴ 16, 2019
ሕንድ
በሕንድ ምዕራባዊ ክፍል የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከሰተ
የዜና ዘገባዎች እንደገለጹት በሕንድ ምዕራባዊ ክፍል የደረሰ የጎርፍ መጥለቅለቅ በጉጅራት፣ በማሃራሽትራ፣ በካርናታካ እና በኬራላ ግዛቶች ቢያንስ የ169 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።
የሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ሪፖርት እንዳደረገው በጎርፍ መጥለቅለቁ ምክንያት የሞተ ወይም የቆሰለ የይሖዋ ምሥክር የለም። ቅርንጫፍ ቢሮው የሚከተለውን ዝርዝር መረጃ ሰጥቷል።
ጉጅራት፦ ጎርፉ በቫዶዳራ ከተማ ውስጥ በሚኖሩ 145 አስፋፊዎች ላይ የንብረት ጉዳት አስከትሏል። በቫዶዳራ የሚገኘው የጉጅራቲ የርቀት የትርጉም ቢሮ ምንም ጉዳት አልደረሰበትም።
ማሃራሽትራ፦ በሙምባይ የስድስት ቤተሰቦች መኖሪያ ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከሙምባይ በስተ ደቡብ ምሥራቅ 378 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በሳንግሊ ከተማ 25 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። በአቅራቢያው በሚገኝ ከተማ የሚኖሩ ወንድሞች እነዚህን አስፋፊዎች ተቀብለዋቸዋል።
ካርናታካ፦ ስድስት ቤተሰቦች በጎርፉ ምክንያት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኘው በዚህ ግዛት ቢሆንም በኃይለኛው ዝናብም ሆነ በጎርፉ ጉዳት አልደረሰበትም።
ኬራላ፦ አንድ መቶ ገደማ የሚሆኑ ቤተሰቦች አካባቢያቸውን በመልቀቅ ከፍ ብሎ በሚገኝ አካባቢ ከሚኖሩ ወንድሞች ጋር ለጊዜው ተጠልለዋል። የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው ሁኔታውን እየገመገመ ነው።
ቅርንጫፍ ቢሮው በአደጋው በተጠቁ አካባቢዎች እርዳታ የመስጠቱን ሥራ እያስተባበረ ነው። የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ዲፓርትመንት የመስክ አገልጋዮች የጉዳቱን መጠን ለማወቅ ብሎም ለወንድሞቻችንና እህቶቻችን እርዳታ ለመስጠት በትጋት እየሠሩ ነው። ይህም እንደ መጠጥ ውኃ ያሉትን መሠረታዊ ነገሮች በማከፋፈል ቁሳዊ እርዳታ መስጠትን እንዲሁም መንፈሳዊ ማበረታቻ ማካፈልን ይጨምራል።
ይሖዋ በጎርፍ መጥለቅለቁ የተጎዱ ወንድሞቻችንን መርዳቱን እንዲቀጥል እንጸልያለን። የተፈጥሮ አደጋዎች ጠፍተው “ብዙ ሰላም” የሚሰፍንበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን።—መዝሙር 37:11