ኅዳር 1, 2023
ሕንድ
በሕንድ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የክልል ስብሰባ በተካሄደበት ቦታ ከተከሰተው ፍንዳታ ወዲህ እርስ በርስ እየተደጋገፉ ነው
እሁድ፣ ጥቅምት 29, 2023 በኬረላ፣ ሕንድ የክልል ስብሰባ በሚካሄድበት ቦታ የቦንብ ፍንዳታ እንደተከሰተ በjw.org ሰበር ዜና ላይ ተገልጾ ነበር። የሚያሳዝነው መጀመሪያ ላይ ከሞቱት ሁለት እህቶች በተጨማሪ አንዲት የ12 ዓመት ልጅ በደረሰባት ጉዳት የተነሳ ሕይወቷ አልፏል። ሌሎች 55 ወንድሞችና እህቶች የተጎዱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ከባድ ቃጠሎ ደርሶባቸዋል።
በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሦስት እህቶችና ሁለት ወንድሞች በሆስፒታል ክትትል እየተደረገላቸው ነው። የአካባቢው ፖሊሶች፣ ጠዋት 3:40 አካባቢ የመክፈቻው ጸሎት እየተደረገ ሳለ ቢያንስ ሦስት ቦንቦች እንደፈነዱ አረጋግጠዋል። ይህን አሰቃቂ ድርጊት እንደፈጸመ የተጠረጠረው ግለሰብ በአሁኑ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት ይገኛል።
በአፋጣኝ በሥፍራው በመገኘት እርዳታ ላበረከቱት የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞችና የተጎዱትን እየተንከባከቡ ላሉት የሆስፒታል ሠራተኞች በጣም አመስጋኞች ነን።
በስብሰባው ላይ የተገኙት ወንድሞችና እህቶች የእምነት ባልንጀሮቻቸው ባሳዩአቸው ፍቅርና በሰጧቸው ማበረታቻ ልባቸው በጥልቅ ተነክቷል። ፍንዳታው በተከሰተበት ወቅት አዳራሹ ውስጥ የነበረች እህት እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ወዲያውኑ ወደ ይሖዋ መጸለይ ጀመርኩ። አስተናጋጆቹ እንዲሁም ሌሎች ወንድሞች በጣም ተንከባክበውናል፤ እንዲሁም ደህንነታችን የተጠበቀ እንዲሆን ፈጣን እርምጃ ወስደዋል። እነሱ ያደረጉልን ነገር ይሖዋ ለእያንዳንዳችን ያለውን ፍቅርና አሳቢነት የሚያሳይ ነው።”
የሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና በአካባቢው ያሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች በአደጋው የተጎዱትን በመንፈሳዊ እያበረታቱና በሚያስፈልጋቸው ነገር እየደገፏቸው ይገኛሉ። በኬረላ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች ለማጽናናት ወደዚያ የሄደ በቅርንጫፍ ቢሮው የሚያገለግል አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች በደረሰባቸው አሰቃቂ ነገር የተነሳ ከፍተኛ ድንጋጤና ሥቃይ ላይ ቢሆኑም አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው መሆኑ በጣም አበረታቶኛል። አብዛኞቹን የማነጋገር አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። በይሖዋ ምን ያህል እንደሚታመኑ በገዛ ዓይኔ ማየቴ እምነቴን አጠናክሮታል።”
በዓለም ዙሪያ የምንገኝ የይሖዋ ሕዝቦች፣ በሕንድ በተፈጸመው በዚህ አስከፊ ጥቃት ለተጎዱት ወንድሞችና እህቶች ቤተሰቦች እንዲሁም ይህ አደጋ ለሚነካቸው ሁሉ እንጸልያለን። መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ዓመፅ፣ መከራና ሞት የማይኖርበት ጊዜ እንደሚመጣ የገባውን ቃል ማሰባችን መጽናኛና ሰላም ይሰጠናል። እስከዚያው ግን በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመናችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።—መዝሙር 56:3