በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 30, 2020
ሕንድ

አዲስ ዓለም ትርጉም በሦስት የሕንድ ቋንቋዎች ወጣ

አዲስ ዓለም ትርጉም በሦስት የሕንድ ቋንቋዎች ወጣ

እሁድ፣ ጥቅምት 25, 2020 አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሦስት የሕንድ ቋንቋዎች ማለትም በጉጅራቲ፣ በካነዳ እና በፑንጃቢ ወጣ። አስቀድመው በተቀረጹ ንግግሮች አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱሶቹ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት መውጣታቸው ተገለጸ። አስፋፊዎች ፕሮግራሙን በየቤታቸው ሆነው ተከታትለዋል። ከዚያም ፕሮግራሙ እንዳለቀ መጽሐፍ ቅዱሱን በራሳቸው ቋንቋ ማውረድ ችለዋል።

ጉጅራቲ

በዓለም ዙሪያ ያሉ ወደ 61 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ጉጅራቲ እንደሚናገሩ ይገመታል።

ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማጠናቀቅ በሁለት ቡድኖች የታቀፉ ስድስት ተርጓሚዎች ለሰባት ዓመት ያህል ሠርተዋል። የትርጉም ቡድኑ አባል የሆነች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መውጣቱ ልባችን በደስታ እንዲሞላ አድርጓል። ትርጉሙ የተዘጋጀው ትናንሽ ልጆች እንኳ ሊረዱት በሚችሉት ቋንቋ ነው።”

ሌላ ተርጓሚም እንዲህ ብላለች፦ “ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የይሖዋ ስም በበኩረ ጽሑፉ ላይ በነበረባቸው ቦታዎች ሁሉ እንዲገባ አድርጓል። ወንድሞችና እህቶች ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በግል ጥናታቸው ላይ መጠቀማቸው እምነታቸውን እንደሚያጠናክረው ምንም ጥርጥር የለውም።”

ይህ ለመረዳት ቀላል የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በአንባቢዎቹ አእምሮ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርና “የዋሆች” የይሖዋን መንገዶች እንዲማሩ እንደሚረዳ እንተማመናለን።—መዝሙር 25:9

ካነዳ

ለንግግርና ለጽሑፍ በሚያገለግለው የካነዳ ቋንቋ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። የንግግሩ ቋንቋ ከቦታ ቦታ ይለያያል። ስለዚህ ተርጓሚዎቹ ያጋጠማቸው ትልቁ ፈተና የመጽሐፍ ቅዱሱን መልእክት ሳያዛቡ ሐሳቡን ቀላል በሆነና ለዛውን በጠበቀ መንገድ ማስተላለፍ ነው።

የትርጉም ሥራውን ለማጠናቀቅ ከሰባት ዓመት በላይ ፈጅቷል። በአጠቃላይ አሥር ተርጓሚዎች በዚህ ሥራ ተካፍለዋል። አንዲት ተርጓሚ እንዲህ ብላለች፦ “በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ይህ መጽሐፍ ቅዱስ እስከ 2021 ድረስ የሚወጣ አልመሰለኝም ነበር። ሆኖም የይሖዋን ሥራ ሊያስቆም የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ተገንዝቤያለሁ።”

የትርጉም ቡድኑ አባል የሆነ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አሁን የካነዳ ቋንቋ ተናጋሪዎች የይሖዋን ቃል በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማንበብና የይሖዋን ስም ቀድሞ በነበረበት ቦታ ሁሉ ላይ ማግኘት ይችላሉ፤ ይህን ማወቅ በጣም ያስደስታል!”

ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ ያሉትን ከ2,800 የሚበልጡ የካነዳ ተናጋሪ አስፋፊዎች በእጅጉ እንደሚጠቅም እንተማመናለን። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ወደ 46 ሚሊዮን የሚጠጉ የቋንቋው ተናጋሪዎች “የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት” ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ እንዲያስተውሉ እንደሚረዳ እርግጠኞች ነን።—ሮም 11:33

ፑንጃቢ

የፑንጃቢ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ቡድን፣ ስድስት ተርጓሚዎችን ያካተተ ነው፤ እነዚህ ተርጓሚዎች በዚህ ፕሮጀክት ላይ ለ12 ዓመት ያህል ሠርተዋል። ይህ ትርጉም በሕንድም ሆነ በሌሎች አገሮች ያሉትን ከ100 ሚሊዮን የሚበልጡ የቋንቋውን ተናጋሪዎች ይጠቅማል።

አንዲት ተርጓሚ እንዲህ ብላለች፦ “አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ አድርገናል። ሥራው እንዲጠናቀቅ ከኋላችን ሆኖ የደገፈን ይሖዋ ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የወንድሞቻችንን እምነት እንደሚያጠናክር፣ የተጨነቀ ልባቸውን እንደሚያረጋጋና ወደፊት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተሻለ ሁኔታ እንዲወጡ እንደሚረዳ እርግጠኞች ነን።”

ሌላ ተርጓሚ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ አስደሳች ይሆንላቸዋል፤ በተለይ የግጥም ይዘት ያላቸውን መጻሕፍት ይወዷቸዋል። ምርምር ለማድረግ እንዲረዱ ከተዘጋጁት የዚህ ትርጉም ክፍሎችም ብዙ ጥቅም ያገኛሉ።”

እኛም ከወንድሞቻችን ጋር አብረን በመሆን ‘ዘርዝረን ለማንጨርሳቸው ድንቅ ሥራዎቹ’ ይሖዋን እናወድሰዋለን።—መዝሙር 40:5