በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 31, 2019
ሕንድ

የይሖዋ ምሥክሮች ሕንድ ውስጥ በቴሉጉ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ አወጡ

የይሖዋ ምሥክሮች ሕንድ ውስጥ በቴሉጉ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ አወጡ

ጥቅምት 25, 2019 ሃይድራባድ፣ ሕንድ በሚገኘው ሃይድራባድ ኢንተናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር በተደረገው የክልል ስብሰባ ላይ የሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አሾክ ፓቴል አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በቴሉጉ ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ።

ሕንድ ውስጥ የቴሉጉ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ 91.9 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች አሉ፤ በመሆኑም ከሂንዲና ከቤንጋሊ ቀጥሎ ሕንድ ውስጥ በሦስተኛ ደረጃ በብዛት የሚነገረው ቋንቋ ቴሉጉ ነው። በአሁኑ ጊዜ በቴሉጉ ቋንቋ ክልል ውስጥ የሚያገለግሉ አስፋፊዎች ቁጥር 6,000 ገደማ ነው፤ ሆኖም በክልል ስብሰባው ላይ የተገኙት ተሰብሳቢዎች አጠቃላይ ቁጥር 8,868 ነበር። ይህ አኃዝ በቴሉጉ ቋንቋ ክልል ውስጥ ብዙ እድገት እንደሚጠበቅ የሚያሳይ ነው፤ እንዲያውም በዚህ ዓመት ብቻ ሁለት ወረዳዎች ተመሥርተዋል።

አምስት ዓመት በወሰደው የቴሉጉ መጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ ላይ የተካፈለ አንድ ወንድም ሌሎቹ የቴሉጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጥንታዊ ቃላትን ስለሚጠቀሙ በተለይ ወጣቶች የሚያነቡትን ነገር ለመረዳት ይቸገሩ እንደነበር ገልጿል። አክሎም “በዚህ አዲስ ትርጉም አማካኝነት ይሖዋ ወጣቶችን ቀላልና ግልጽ በሆነ ቋንቋ እያነጋገራቸው ነው ማለት ይቻላል” ብሏል። አንዲት ሌላ ተርጓሚ ደግሞ “አገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች ከዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቅስ ስናነብላቸው ወዲያውኑ መልእክቱን መረዳት ይችላሉ” በማለት ተናግራለች።

ከዚህም በተጨማሪ በአብዛኞቹ የቴሉጉ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም አይገኝም፤ በመሆኑም አዲስ ዓለም ትርጉም የቴሉጉ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ስም እንዲያውቁ ይረዳቸዋል። ከዚህም ሌላ ሌሎቹ የቴሉጉ መጽሐፍ ቅዱሶች ነፍስ እና መንፈስ እንደሚሉት ያሉ ቃላትን ከሂንዱ እምነት ጋር በሚስማማ መንገድ ተርጉመዋቸዋል፤ አዲስ ዓለም ትርጉም ግን አንባቢዎቹ የእነዚህን ቃላት ትክክለኛ ፍቺ እንዲያውቁ ይረዳቸዋል።

አንድ አስፋፊ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የቴሉጉ ቋንቋ ተናጋሪዎች የይሖዋን ፍቅር ከምንጊዜውም ይበልጥ መረዳት እንዲችሉ የሚረዳቸው ይመስለኛል!” አዲስ ዓለም ትርጉም የቴሉጉ ቋንቋ ተናጋሪዎች ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቀምሰው እንዲያዩ’ እንደሚረዳቸው ጥያቄ የለውም።—መዝሙር 34:8