ግንቦት 29, 2020
ማላዊ
ማላዊ ውስጥ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የሚሰራጩት የጉባኤ ስብሰባዎች በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ተደራሽ ሆነዋል
የማላዊ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ የጉባኤ ስብሰባ ፕሮግራሞች በአገሪቱ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች እንዲሰራጩ ዝግጅት አድርጓል። ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችም ከእነዚህ ስርጭቶች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። ማላዊ ውስጥ ከ100,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ያሉ ቢሆንም በየሳምንቱ ቅዳሜ ወይም እሁድ ላይ የሚተላለፈውን የቴሌቭዥን ስርጭት ሁለት ሚሊዮን ሰዎች፣ የሬዲዮ ስርጭቱን ደግሞ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች እንደሚከታተሉ የማሰራጫ ጣቢያዎቹ ይገምታሉ።
በብዙ አገሮች ውስጥ እንዳሉ ወንድሞቻችን ሁሉ በማላዊ ያሉ ወንድሞቻችንም የአካላዊ ርቀት ደንቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ሲሉ በስብሰባ አዳራሾች ውስጥ መሰብሰብ አቁመዋል። ሁሉም የጉባኤ አስፋፊዎች ማለት ይቻላል፣ ቴሌቪዥን ወይም ሬዲዮ አላቸው። በመሆኑም ይህ ዝግጅት የኢንተርኔት አገልግሎት ለማግኘት አቅሙ የሌላቸው ወይም በቪዲዮ ኮንፍረንሲንግ አማካኝነት መሰብሰብ የማይችሉ ሰዎች የጉባኤ ስብሰባዎችን እንዲከታተሉ አስችሏል።
ስብሰባዎቹ የሚሰራጩት የአገሪቱ ዋነኛ ቋንቋ በሆነው በቺቼዋ ነው። ሙሉው የቴሌቪዥን ፕሮግራም በማላዊ ምልክት ቋንቋ ይተረጎማል። ሕዝባዊ ስብሰባው፣ ከሕዝብ ንግግር በተጨማሪ ቪዲዮዎችን ወይም ድራማዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦችን ያካተተ ነው። በፕሮግራሙ መጨረሻ ላይ ተመልካቾችና አድማጮች በሌሎች ቋንቋዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት jw.orgን እንዲመለከቱ ግብዣ ይቀርብላቸዋል።
እነዚህ ስርጭቶች አንዳንድ ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲያስተካክሉ ረድተዋል። አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ባለፉት ሳምንታት በሬዲዮ ያስተላለፋችሁትን ስብከት ሳዳምጥ ነበር። ሰዎች ስለ እናንተ ለሚያሰራጩት የሐሰት ወሬ አጥጋቢ መልስ የሚሰጥ ነው። ስብከታችሁ ከሌሎች ሃይማኖቶች በተለየ የሰዎችን ልብ የሚነካ ነው!” ይህ ሰውና ቤተሰቡ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል።
በማላዊ ቅርንጫፍ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዴስክ ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ የሚያስተባብረው ኦገስቲን ሲሞ እንዲህ ብሏል፦ “ስርጭቶቹ ወንድሞች መንፈሳዊ ልማዳቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ በእጅጉ ረድተዋል። በተጨማሪም በርካታ ሰዎች፣ የምናስተምረውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ማወቅ እንዲችሉ በር ከፍተዋል። ማላዊ ውስጥ ሁኔታዎች ሲስተካከሉ ብዙ አዳዲስ ሰዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ አብረውን እንደሚሰበሰቡ ተስፋ እናደርጋለን።”
በማላዊ ያሉ የእምነት ባልንጀሮቻችንም ሆኑ ሌሎች ሰዎች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በመንፈሳዊ በሚገባ እየተመገቡ እንደሆነ ማወቅ በጣም ያስደስተናል። እንዲሁም ሁሉም ሰው በመንፈሳዊ እንዲመገብ ዝግጅት ላደረገው ‘ለታማኙ ባሪያ’ ያለንን አድናቆት ይጨምርልናል።—ማቴዎስ 24:45