በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በአሁኑ ጊዜ በሊሎንግዌ፣ ማላዊ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ። ውስጠኛዎቹ ፎቶግራፎች (ከላይ በስተ ግራ አንስቶ ዙሪያውን)፦ በማላዊ የመጀመሪያው የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ የነበረው ወንድም ቢል ማክሉኪ፤ በ1967 ባለሥልጣናት ቅርንጫፍ ቢሮውን ሲያሽጉ፤ አንዲት እህት በአሁኑ ጊዜ በስብከቱ ሥራ በደስታ ስትካፈል

ታኅሣሥ 28, 2023
ማላዊ

በማላዊ የመጀመሪያው ቅርንጫፍ ቢሮ ከተቋቋመ 75 ዓመታት ተቆጠሩ

አስደናቂ ጽናት የታየበት ታሪክ

በማላዊ የመጀመሪያው ቅርንጫፍ ቢሮ ከተቋቋመ 75 ዓመታት ተቆጠሩ

የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በማላዊ በምትገኘው ብላንታየር ከተማ የተቋቋመው በ1948 ማለትም የዛሬ 75 ዓመት ነበር።

ከዚያ በፊት በማላዊ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ የሚከታተለው የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ነበር። ከ1930ዎቹ አንስቶ በማላዊ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ቁጥር እየጨመረ ሄዶ 1934 ላይ 28 ብቻ የነበሩት አስፋፊዎች በ1948 ከ5,600 በላይ ሆኑ። የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ወንድሞች በብላንታየር ከተማ አንድ አነስተኛ አፓርታማ ተከራይተው መስከረም 1, 1948 በዚያ የመጀመሪያው ቅርንጫፍ ቢሮ ተከፈተ። በ1958 በብላንታየር አቅራቢያ አዲስ የቤቴል ሕንፃ እስከተገነባበት ጊዜ ድረስ ይህ ቢሮ አገልግሎት መስጠቱን ቀጥሏል።

በስተ ግራ፦ የቺቼዋ እና የቺቱምቡካ ቋንቋ ተርጓሚዎች በ1958 በማላዊ ከተገነባው ቅርንጫፍ ቢሮ ውጭ የተነሱት ፎቶግራፍ። ከእነሱ መካከል በአሁኑ ጊዜ የማላዊ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም ባስቶን ንዪሬንዳ (ክብ የተደረገበት) ይገኝበታል። በስተ ቀኝ፦ የ80 ዓመቱ ወንድም ባስቶን እና ባለቤቱ ቫዮሌት በአሁኑ ጊዜ

አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ማለትም ጥቅምት 1967 የማላዊ ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ አገዱ። በዚህም የተነሳ ቅርንጫፍ ቢሮው ታሸገ። ያም ሆኖ በማላዊ ያሉ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በመላው አገሪቱ የስብከቱን ሥራ ማደራጀታቸውንና የእምነት ባልንጀሮቻቸውን መርዳታቸውን ቀጠሉ። ከዚያ በኋላ ባለው ወደ 26 ዓመት የሚጠጋ ጊዜ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋም በመያዛቸው ከባድ ስደትና አሰቃቂ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ታስረዋል፤ ሥቃይ ደርሶባቸዋል፤ አልፎ ተርፎም ተገድለዋል። አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች እንደ ሞዛምቢክ፣ ዚምባብዌ እና ዛምቢያ ወዳሉ አጎራባች አገራት ለመሸሽ መርጠዋል።

ወንድሞችና እህቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ቺቼዋ ሲተረጉሙ

በመጨረሻም ነሐሴ 12, 1993 እገዳው ተነሳ። በእገዳው ወቅት በማላዊ የሚካሄደውን ሥራ ለተወሰኑ ዓመታት ሲከታተሉ የነበሩት በዛምቢያ የነበሩ ወንድሞች፣ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ሥራውን በማደራጀቱ ሥራ እገዛ አበርክተዋል። ከዚያም ወንድሞቻችን በሊሎንግዌ ከተማ ሁለት ቤቶችን የገዙ ሲሆን እነዚህ ቤቶች በማላዊ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ሆነው ማገልገል ጀመሩ። በ1994 የበላይ አካሉ፣ ወንድሞች በአገሪቱ አዲስ የቤቴል ሕንፃዎች ለመገንባት ምቹ ቦታ እንዲፈልጉ ፈቃድ ሰጠ። ግንቦት 19, 2001 በተካሄደው በእነዚህ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች ውሰና ላይ ከ2,000 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ለአሥርተ ዓመታት የደረሰባቸውን ስደት በጽናት የተቋቋሙ ናቸው። በውሰና ፕሮግራሙ ላይ ከተገኙት ወንድሞች መካከል በእገዳው ወቅት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለገለው ወንድም ትሮፊም ንሶምባ ይገኝበታል። ወንድም ንሶምባ አዲሶቹን የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎችና በማላዊ የታየውን መንፈሳዊ እድገት አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ከይሖዋ ያገኘናቸው እነዚህ በረከቶች በጣም አስደናቂ ከመሆናቸው የተነሳ እኔና [ባለቤቴ] ሕልም እንጂ በእውን የተፈጸሙ አይመስለንም!”

በዛሬው ጊዜ በማላዊ ባሉ 1,924 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ከ109,000 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል በሊሎንግዌ በሚገኘው የማላዊ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግሉት 225 ቤቴላውያን ይገኙበታል፤ በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ወደ ሰባት ቋንቋዎች ይተረጎማሉ።

በአሁኑ ጊዜ በማላዊ ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ከሚገኙት 109,000 ወንድሞችና እህቶች መካከል አንዳንዶቹ

ይሖዋ ለብዙ አሥርተ ዓመታት በመጽናት ራሳቸውን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገው ያቀረቡትን በማላዊ ያሉ ውድ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መባረኩን እንዲቀጥል እንጸልያለን።​—2 ቆሮንቶስ 6:4