ግንቦት 5, 2022
ማላዊ
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቺያኦ ቋንቋ ወጣ
የማላዊ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ፍራንክ ማድሰን ሚያዝያ 24, 2022 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቺያኦ ቋንቋ በዲጂታል ፎርማት መውጣቱን አበሰረ። አስቀድሞ የተቀረጸው ፕሮግራም በሳተላይት ቴሌቪዥን እንዲሁም እንደ JW ቦክስ እና JW ስትሪም ባሉ ሌሎች መንገዶች የተሰራጨ ሲሆን ከ148,000 በላይ ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ማግኘት ይቻላል።
በቺያኦ ቋንቋ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ከ2014 አንስቶ ይገኝ ነበር። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሙ አንዳንድ ስህተቶች ያሉት ከመሆኑም ሌላ በመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ጊዜያት የሚገኘውን ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ሙሉ በሙሉ አውጥቶታል።
በመሆኑም በርካታ አስፋፊዎች እነዚህን መጽሐፍ ቅዱሶች በአገልግሎት ላይ መጠቀም ያስቸግራቸው ነበር። አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ጊዜ የምናጠፋው፣ የአምላክ ስም ያለውን አስፈላጊነት በማስረዳት ሳይሆን የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኘው ለምን እንደሆነ በማብራራት ነው።” ለምሳሌ በቺያኦ የተዘጋጀ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ማቴዎስ 22:44ን “ጌታ ጌታዬን” በማለት ተርጉሞታል። አዲስ ዓለም ትርጉም ግን “ይሖዋ ጌታዬን” በማለት በትክክል አስቀምጦታል።
ሌላ ተርጓሚ ደግሞ ይህ አዲስ ትርጉም ያለውን ጠቀሜታ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በቺያኦ የተዘጋጀው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ግልጽና ለመረዳት ቀላል በመሆኑ ሰዎች መልእክቱን ወዲያውኑ መረዳት ይችላሉ፤ እንዲሁም የተማሩትን ነገር በሥራ ላይ ለማዋል ይነሳሳሉ።”
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቺያኦ ተናጋሪዎች “በመላው ምድር ላይ ልዑል” የሆነውን የይሖዋን ስም እንዲያውቁና ወደ እሱ እንዲቀርቡ የሚረዳ መጽሐፍ ቅዱስ በመውጣቱ በጣም ተደስተናል።—መዝሙር 83:18