ሰኔ 9, 2022
ማሌዥያ
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በኢባን ቋንቋ ወጣ
ሰኔ 5, 2022 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በኢባን ቋንቋ ወጣ።በርካታ ወንድሞችና እህቶች አስቀድሞ የተቀረጸውን ፕሮግራም በስብሰባ አዳራሽ ተገኝተው ተከታትለዋል። ሌሎች አስፋፊዎች ደግሞ ፕሮግራሙን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተመልክተዋል። የታተመው ቅጂ ሐምሌ ወይም ነሐሴ 2022 ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ቡድኑ ሥራውን ሲያከናውን፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚሠራባቸውን የኢባን ቀበሌኛዎች ግምት ውስጥ ማስገባት ነበረበት። በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አንባቢዎች፣ ተርጓሚዎቹ አብዛኛው የኢባን ተናጋሪ የሚረዳውን አገላለጽ እንዲጠቀሙ አግዘዋቸዋል።
ይህ ትርጉም፣ አስፋፊዎች አገልግሎት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በትክክለኛው መንገድ እንዲያብራሩም ይረዳቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ከዚህ ቀደም አስፋፊዎች ዮሐንስ 4:24ን ለሰዎች ለማብራራት ይቸገሩ ነበር፤ ጥቅሱ “[አምላክን] የሚያመልኩትም በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል” ይላል። በኢባን የተዘጋጁ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “መንፈስ” የሚለውን ቃል “የሙታን መንፈስ” ብለው በተሳሳተ መንገድ ተርጉመውታል። ይህም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አምላክን እንዴት ማምለክ እንዳለባቸው ግራ እንዲጋቡ አድርጓቸው ነበር።
የትርጉም ቡድኑ አባል የሆነ አንድ ወንድም ይህ ትርጉም ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቋንቋችን መዘጋጀቱ ይሖዋ ሁሉንም የሰው ልጆች ምን ያህል እንደሚወድ በግልጽ የሚያሳይ ነው።”
በቅርቡ የወጣው ይህ ትርጉም ኢባን ተናጋሪ የሆኑ በርካታ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ለመረዳት፣ ወደ አምላክ ለመቅረብና ለይሖዋ ስም ውዳሴ ለማቅረብ እንዲረዳቸው እንጸልያለን።—መዝሙር 117:1