የካቲት 7, 2022
ማልታ
የይሖዋ ምሥክሮች በማልታ ሕጋዊ እውቅና ተሰጣቸው
የማልታ የይሖዋ ምሥክሮች (JW-ማልታ) የተባለ አዲስ ሕጋዊ ድርጅት በቅርቡ በአገሪቱ ውስጥ ሕጋዊ እውቅና ተሰጠው። JW-ማልታ ታኅሣሥ 28, 2021 የምዝገባ ምሥክር ወረቀት ተሰጥቶት ሕጋዊ ሰውነት a አገኘ።
የይሖዋ ምሥክሮች ከ1970ዎቹ አንስቶ በማልታ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ሆኖም ጉባኤዎቹ ለአሥርተ ዓመታት ምንም ሕጋዊ እውቅና አልነበራቸውም ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት ጉባኤዎች የንብረት ባለቤት መሆንም ሆነ የባንክ ሒሳብ መክፈት በጣም ከባድ ሆኖባቸው ነበር። በ1994 ዓለም አቀፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር (IBSA) በማልታ ሙሉ እውቅና የሌለው ማኅበር ሆነ። ይህም ዓለም አቀፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር አንዳንድ መብቶች እንዲያገኝ ያስቻለ ቢሆንም መብቶቹ በጣም የተገደቡ ነበሩ። JW-ማልታ በቅርቡ እውቅና ማግኘቱ በማልታ ያለው የአገር ቢሮም ሆነ ጉባኤዎቹ ሥራቸውን በቀላሉ እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል።
የማልታ የአገር ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጆ ማግሪ በቅርቡ የተገኘውን ሕጋዊ እውቅና አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ይህን ሕጋዊ እውቅና እንድናገኝ እንዴት እንደረዳን ማየታችን እምነታችንን አጠናክሮታል። ሕጋዊ እውቅናውን ማግኘት እንድንችል በብሪታንያ እና በዋናው መሥሪያ ቤት በሚገኙት የሕግ ክፍሎች ተጠቅሞ ረድቶናል። የይሖዋ ስም በተካተተበት በዚህ አዲስ ሕጋዊ ድርጅት አማካኝነት ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማራመድና ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማወደስ በመቻላችን በጣም ተደስተናል።”
በአሁኑ ወቅት በማልታ በ11 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ከ800 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት በማልታ ያስጀመረው “ስለ አምላክ መንግሥት” የመስበኩ ሥራ “ያለምንም እንቅፋት” መቀጠል በመቻሉ ደስተኞች ነን።—የሐዋርያት ሥራ 28:1, 30, 31
a ከሕግ አንጻር ግለሰቦች፣ ኩባንያዎችና ሌሎች አካላት “ሕጋዊ ሰውነት” ማግኘት ይችላሉ።