ጥቅምት 19, 2023
ማይክሮኔዥያ
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቹኪዝ ቋንቋ ወጣ
የማይክሮኔዥያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ካርሊቶ ዴላ ክሩዝ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቹኪዝ ቋንቋ መውጣቱን ጥቅምት 1, 2023 አብስሯል። የምሥራቹ የተነገረው በቹክ፣ ማይክሮኔዥያ በተደረገውና 83 ሰዎች በተገኙበት ልዩ ስብሰባ ላይ ነው። በጉዋም እና በዩናይትድ ስቴትስ ባሉ በቹክ ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችና ቡድኖች ውስጥ ያሉትን ጨምሮ ሌሎች 435 ሰዎች ፕሮግራሙን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተከታትለዋል። መጽሐፉ እንደወጣ ወዲያውኑ ኤሌክትሮኒክ ቅጂውን ማውረድ ተችሏል። የታተመው ቅጂ ደግሞ ጥር 2024 ይሰራጫል።
ቹኪዝ በዋነኝነት የሚነገረው በምዕራብ ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በሚገኙትና የማይክሮኔዥያ ፌዴራላዊ ግዛቶች ክፍል በሆኑት በቹክ ደሴቶች ውስጥ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻቸውን ወደ ቹኪዝ ቋንቋ መተርጎም የጀመሩት በ1978 ነበር። በአሁኑ ወቅት በቹክ ደሴቶች በሚገኙ በቹኪዝ ቋንቋ የሚመሩ ሁለት ጉባኤዎች ውስጥ 180 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች ያገለግላሉ፤ ከዚህ በተጨማሪ በጉዋም ደሴት አንድ ጉባኤ በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ አንድ ጉባኤ፣ ሦስት ቡድኖች እና አንድ ቅድመ ቡድን ይገኛሉ።
በቹኪዝ ቋንቋ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ያሉ ቢሆንም ብዙዎቹ ይሖዋ የሚለውን የአምላክን ስም አልያዙም። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም መለኮታዊውን ስም በትክክለኛው ቦታ መልሶ አስገብቷል። ወንድም ዴላ ክሩዝ እንዲህ በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፦ “ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ብዙ ቹኪዝ ተናጋሪዎች የአምላክን ስም እንዲያውቁ ብሎም ወደ እሱ እንዲቀርቡ እንደሚረዳቸው እርግጠኛ ነኝ።”
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቹኪዝ ቋንቋ መውጣቱ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ብዙ ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ የሚረዳቸው በመሆኑ ተደስተናል።—ሥራ 13:48