በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥር 17, 2023
ሜክሲኮ

ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በሜክሲኮ ምልክት ቋንቋ ወጣ

ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በሜክሲኮ ምልክት ቋንቋ ወጣ

የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አርማንዶ ኦቾዋ ጥር 1, 2023 በተካሄደ ልዩ ፕሮግራም ላይ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሜክሲኮ ምልክት ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል፤ መጽሐፍ ቅዱሱ በ​jw.org እና በ​JW የምልክት ቋንቋ አፕሊኬሽን ላይ እንደተለቀቀም ገልጿል። ልዩ ፕሮግራሙ የተካሄደው በኤል ቴሆኮቴ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ነው።

አንድ ወንድም (በስተ ቀኝ) ማየትና መስማት ለተሳነው አስፋፊ በዳሰሳ የምልክት ቋንቋ ልዩ ፕሮግራሙን ሲያስተረጉም

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከጀመረ ወዲህ በማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ ብዙ ሰዎች በአካል የተገኙበት ስብሰባ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው ነው። ፕሮግራሙ በተካሄደበት አዳራሽ ውስጥ 2,317 ወንድሞችና እህቶች በአካል ተገኝተዋል። ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከመላው ሜክሲኮ በተለያዩ የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችና የጉባኤ ስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ሆነው ፕሮግራሙን በኢንተርኔት በቀጥታ ተከታትለዋል።

ከታዳሚዎቹ መካከል የአሜሪካና የሜክሲኮ ምልክት ቋንቋዎች ምሁር የሆኑት አቶ ሰርኺዮ ፔኛ እና የዩካታን ግዛት የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ማሪያ ቴሬዛ ባዝኬስ ይገኙበታል።

አቶ ፔኛ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፦ “የሜክሲኮ የይሖዋ ምሥክሮች አድናቆታችን ይገባችኋል። ከጥር 1, 2023 ጀምሮ መስማት የተሳናቸው ሰዎች . . . ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በሜክሲኮ ምልክት ቋንቋ ማግኘት ችለዋል። ‘ድንቅ የጥበብ ሥራ ነው’ ብል ማጋነን አይደለም።”

በሜክሲኮ ምልክት ቋንቋ አዲስ ዓለም ትርጉምን የማዘጋጀት ሥራ የተጀመረው ነሐሴ 2008 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመተርጎም ነው። ባለፉት 14 ዓመታት የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ተራ በተራ ሲወጡ ቆይተዋል። በሜክሲኮ ምልክት ቋንቋ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ሲወጣ ይህ የመጀመሪያው ነው።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም እንኳ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በመውጣታቸው፣ መስማት የተሳናቸው አስፋፊዎች በእጅጉ ተጠቅመዋል። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በወረርሽኙ ወቅት በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በመውጣታቸው በጣም ተደስቻለሁ። ይሖዋ በመንፈሳዊ በሚገባ መግቦናል።”

አንዲት መስማት የተሳናት እህት እንዲህ ብላለች፦ “አዲስ ዓለም ትርጉም በሜክሲኮ ምልክት ቋንቋ ከመውጣቱ በፊት ጥቅሶችን የሚተረጉሙልኝ ወንድሞች ነበሩ። ሆኖም አንደኛው ወንድም አንድን ጥቅስ የሚተረጉምበት መንገድ ከሌላው ይለያል። በመሆኑም ጥቅሶችን በቃል መያዝ እቸገር ነበር። አሁን ግን መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ሌሎችን ማስቸገር አያስፈልገኝም።”

መስማት የተሳናቸውና በከፊል ብቻ የሚሰሙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘታቸው በእጅጉ እንደሚጠቅማቸው እንተማመናለን። ‘የተሻለ ሕይወትና ተስፋ’ እንደሚመጣ የሚያበስረውን ምሥራች ሲያውጁ የይሖዋ በረከት ከእነሱ ጋር እንዲሆን እንጸልያለን።—ኤርምያስ 29:11