በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በኩሊያካን በተነሳው ዓመፅ ወቅት መኪኖች እየተቃጠሉ

ኅዳር 8, 2019
ሜክሲኮ

በኩሊያካን፣ ሜክሲኮ በተነሳው ዓመፅ ምክንያት አንድ የይሖዋ ምሥክር ሕይወቱ አለፈ

በኩሊያካን፣ ሜክሲኮ በተነሳው ዓመፅ ምክንያት አንድ የይሖዋ ምሥክር ሕይወቱ አለፈ

ጥቅምት 17, 2019 በሲናሎዋ፣ ሜክሲኮ በምትገኘው አንድ ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች ባሏት ኩሊያካን ከተማ የሚገኙ ፖሊሶችና የደህንነት ኃይሎች በደንብ ከታጠቁ የዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን አባላት ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው ነበር። በተኩስ ልውውጡ ወቅት የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተዋል፣ መኪናዎች በእሳት ተያይዘዋል እንዲሁም በአካባቢው በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ የነበሩ እስረኞች አምልጠዋል። ባለሥልጣናቱ እንደገለጹት ከሆነ ቢያንስ 14 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። የሚያሳዝነው፣ የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ሪፖርት እንዳደረገው በዓመፁ ወቅት ከሞቱት ሰዎች መካከል ወንድም ኖዌ ቤልትራን ይገኝበታል።

ወንድም ኖዌ ቤልትራን ከሁለት ልጆቹ ጋር

የሦስት ልጆች አባት የሆነው የ39 ዓመቱ ወንድም ኖዌ በሥራ ቦታው ላይ እያለ ተባራሪ ጥይት መታው። በአካባቢው የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ለወንድም ኖዌ ባለቤት ለሮሲዮ እና ለትናንሽ ልጆቿ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማጽናኛና ማበረታቻ እየሰጡ ነው።

ኩሊያካን ውስጥ 80 ጉባኤዎችና 7,000 አስፋፊዎች አሉ። በዓመፁ ወቅት አንዳንድ ጉባኤዎች በሳምንቱ መሃል ስብሰባና በስምሪት ስብሰባዎቻቸው ላይ ጊዜያዊ ማስተካከያ አድርገው ነበር። የተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች ወደ ስብሰባ አዳራሽ መሄድ ስላልቻሉ በሳምንቱ መሃል የሚደረገውን ስብሰባ ከቤታቸው ሆነው ተከታትለዋል። የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በዚህ ድንገተኛ ዓመፅ ምክንያት ስሜታዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ወንድሞችና እህቶች እረኝነት እያደረጉ ነው።

የወንድም ኖዌ ቤልትራንን ሞት በመስማታችን በጣም አዝነናል። ይሖዋ እህት ሮሲዮንና ልጆቿን መንከባከቡን እንዲቀጥል እንጸልያለን። በምድር ላይ ሰላም የሚሰፍንበትንና ሐዘን ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ‘እጅግ የምንደሰትበትን’ ጊዜ እንናፍቃለን።—ማርቆስ 5:42