በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 1, 2019
ሜክሲኮ

አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በማያ ቋንቋ ወጣ

አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በማያ ቋንቋ ወጣ

ጥቅምት 25, 2019 የማያ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ 6,500 ወንድሞችና እህቶች ልዩ ቀን ነበር። ምክንያቱም ይህ ቀን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በማያ ቋንቋ የወጣበት ቀን ነው። የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኢስቴባን ባን ዩካታን፣ ሜክሲኮ ውስጥ በሜሪዳ ከተማ በተደረገው የክልል ስብሰባ ላይ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መውጣቱን አበሰረ። ፕሮግራሙ የተካሄደው በሜሪዳ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ሲሆን በዚያው ከተማ በሚገኘው የፖሊፎረም ሳምና ስታዲየም ለሚገኙ ተሰብሳቢዎችም በቀጥታ ተላልፏል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱ ለስብከቱ ሥራ ትልቅ እርዳታ ያበረክታል፤ ምክንያቱም በሜክሲኮና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 762,000 ገደማ የሚሆኑ የማያ ቋንቋ ተናጋሪዎች አሉ።

ከዚህ በፊት በማያ ቋንቋ የሚገኘው፣ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ብቻ ነበር። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የወጣው ታኅሣሥ 14, 2012 ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ 29,000 ገደማ የሚያህሉ ቅጂዎች ታትመዋል።

በትርጉም ሥራው ከተካፈሉት መካከል አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “በጥቅሉ ሲታይ የማያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አክብሮት አላቸው። ሆኖም ብዙዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን በማያ ቋንቋ አንብቦ መረዳት ይከብዳቸዋል። በመሆኑም ሰዎቹ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚጠቀሙበትንና ለመረዳት ቀላል የሆነ ቋንቋ ለመጠቀም ጥረት አድርገናል።”

የትርጉም ሥራውን ፈታኝ ካደረጉት ነገሮች መካከል አንዱ በየክልሉ የሚነገረው የማያ ቋንቋ የተለያየ መሆኑ ነው። በመሆኑም የአዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሽፋን ቢብሊያ ኢህ ማያ ወይም “የማያ መጽሐፍ ቅዱስ” የሚል ቀላል ርዕስ እንዲኖረው ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ በመጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ በተለያዩ ምድቦች የተቀመጡ በድምሩ ከ6,000 የሚበልጡ የግርጌ ማስታወሻዎች ያሉ ሲሆን አንዱ ምድብ ዋናው ጽሑፍ ሊተረጎም የሚችልባቸውን አማራጮች ይዟል፤ ይህም ሁሉም የማያ ቋንቋ ተናጋሪዎች በመጽሐፍ ቅዱሱ ላይ የሰፈረውን መልእክት በትክክል እንዲረዱ ያስችላል።

ይህ አዲስ ትርጉም የማያ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ወንድሞችና እህቶች ‘በተገቢው ጊዜ ላይ የቀረበ ምግብ’ ከመሆኑም ሌላ ለግል ጥናታቸውም ሆነ ለአገልግሎታቸው ትልቅ እገዛ እንደሚያበረክትላቸው ምንም ጥርጥር የለውም።—ማቴዎስ 24:45