በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 31, 2019
ሜክሲኮ

አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በጾጺል ቋንቋ ወጣ

አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በጾጺል ቋንቋ ወጣ

ጥቅምት 25, 2019 በቺያፓስ፣ ሜክሲኮ በሚገኘው ቱክስትላ ጉቴሬዝ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገ የክልል ስብሰባ ላይ የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አርማንዶ ኦቾዋ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በጾጺል ቋንቋ መውጣቱን አስታወቀ። በሴንትሮ ደ ኮንቬንሲዮኔ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተገኙ ተሰብሳቢዎችም ፕሮግራሙን በቪዲዮ ተከታትለዋል። የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር በድምሩ 3,747 ነበር።

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በጾጺል ቋንቋ የወጣው ታኅሣሥ 26, 2014 ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሱ በቺያፓስ፣ ሜክሲኮ ተራራማና ረባዳማ አካባቢዎች ለሚኖሩ የጾጺል ቋንቋ ተናጋሪዎች ተሰራጭቶ ነበር። በሜክሲኮ ከሚኖሩት የአገሬው ጎሳዎች አባላት የሆኑ ከ16,000,000 የሚበልጡ ነዋሪዎች መካከል 500,000 ገደማ የሚሆኑት የጾጺል ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው፤ የጾጺል ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ 2,814 የይሖዋ ምሥክሮች አሉ።

የጾጺል ቋንቋ ተርጓሚዎች ብዙ ፈተናዎችን ተጋፍጠዋል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በጾጺል ቋንቋ የተዘጋጁት ዓለማዊ መጻሕፍትም ሆኑ መዝገበ ቃላት በጣም ጥቂት ናቸው። በተጨማሪም ቋንቋው ሰባት የተለያዩ ቀበሌኛዎች አሉት። በመሆኑም ተርጓሚዎቹ ሁሉም የጾጺል ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚያውቋቸውን ቃላት ለመጠቀም በጥንቃቄ መምረጥ ይጠበቅባቸው ነበር።

ከተርጓሚዎቹ አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም የያዘ በመሆኑ አንባቢዎቹ በግለሰብ ደረጃ ከአምላክ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ይረዳቸዋል። ከዚህ ትርጉም ውጭ ያሉት ሁለት የጾጺል መጽሐፍ ቅዱሶች መለኮታዊውን ስም ያሰፈሩት ዘፀአት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኝ አንድ የግርጌ ማስታወሻ ላይ ብቻ ነው። በመሆኑም የአምላክን ስም በተገቢው ቦታ ሁሉ ያሰፈረ የመጀመሪያው የጾጺል መጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ዓለም ትርጉም ነው።” የጾጺል ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ አንድ አስፋፊም እንዲህ ብሏል፦ “በጾጺል ቋንቋ የተዘጋጁት ሌሎቹ መጽሐፍ ቅዱሶች በጣም ውድ በመሆናቸው መግዛት የሚችሉት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። ይሄኛውን ትርጉም ግን ማንኛውም ሰው በነፃ ማግኘት ይችላል።”

“መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ” የጾጺል ቋንቋ ተናጋሪዎች በሙሉ አዲስ ከወጣው መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም እንደሚያገኙ ምንም ጥርጥር የለውም።—ማቴዎስ 5:3