በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ነሐሴ 19, 2021
ሜክሲኮ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በሚክስቴክ (ጉዌሬሮ) ወጣ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በሚክስቴክ (ጉዌሬሮ) ወጣ

ነሐሴ 8, 2021 የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሆሴ ኒዬቶ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በሚክስቴክ (ጉዌሬሮ) ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ። መጽሐፍ ቅዱሱ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት መውጣቱ የተገለጸው አስቀድሞ በተቀረጸ ንግግር አማካኝነት ሲሆን 785 ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። ቅርንጫፍ ቢሮው መጽሐፍ ቅዱሱ ኅዳር 2021 መታተም እንደሚጀምርና ታኅሣሥ 2021 ወይም ጥር 2022 ለጉባኤዎች እንደሚሰራጭ ይጠብቃል።

መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱ በተገለጸበት ንግግር ላይ ወንድም ኒዬቶ 1 ቆሮንቶስ 14:9⁠ን ካነበበ በኋላ እንዲህ አለ፦ “የአምላክ ቃል ኃይል አለው፤ ሆኖም ቃሉ የሰዎችን ልብ እንዲነካ ከተፈለገ መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውም ሰው ሊረዳው በሚችል ቋንቋ . . . ማለትም ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በሚጠቀሙበት ቋንቋ መገኘት አለበት።”

ሚክስቴክ (ጉዌሬሮ) ቋንቋ አንድ ባሕርይ አለው፤ ቃላቱ የሚነገሩበት የድምፅ ቅላጼ የቃላቱን ትርጉም ይለውጠዋል። ይህ ቋንቋ በሜክሲኮ በጉዌሬሮ ግዛት በሚኖሩ 150,000 ገደማ ሰዎች እንዲሁም በሌሎች የሜክሲኮና የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ይነገራል።

የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ላዛሮ ጎንዛሌዝ እንዲህ ብሏል፦ “የሚክስቴክ (ጉዌሬሮ) ተናጋሪዎች የሚኖሩት በድህነትና በዓመፅ በሚታመስ አካባቢ ውስጥ ነው። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ደግሞ ሁኔታውን አባብሶታል። ይህም ብዙዎች ‘አምላክ ትቶናል’ ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ሆኖም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማግኘት መቻላቸው ይሖዋ እንደሚያስብላቸው የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው።”

ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከመውጣቱ በፊት በሚክስቴክ (ጉዌሬሮ) የተዘጋጁት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉሞች ሁለት ብቻ ነበሩ። እነዚህ ትርጉሞች ለመረዳት ከባድ ናቸው፤ ምክንያቱም ትርጉሞቹን ያዘጋጁት በሁለት የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ተርጓሚዎች ናቸው። ተርጓሚዎቹ በእነሱ አካባቢ የተለመደውን አገላለጽ ብቻ ስለተጠቀሙ በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የቋንቋው ተናጋሪዎች መጽሐፍ ቅዱሱን አንብበው መረዳት ከባድ ይሆንባቸዋል።

ይህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለመረዳት ቀላል መሆኑን የሚያሳየው አንዱ ምሳሌ ማቴዎስ 5:9 ነው፤ ጥቅሱ “ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው” ይላል። በሚክስቴክ (ጉዌሬሮ) “ሰላም” የሚለው ቃል አቻ ትርጉም የለውም። ትክክለኛውን ትርጉም ለማስተላለፍ ጥቅሱ “ችግሮችን/አለመግባባቶችን ለማስቀረት ጥረት የሚያደርጉ ደስተኞች ናቸው” ተብሎ ተተርጉሟል። ይህ ደግሞ የእንግሊዝኛውን ሐሳብ በትክክል ያስተላልፋል።

አንዱ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “ከምወዳቸው ጥቅሶች አንዱ 1 ጴጥሮስ 1:25 ነው፤ ጥቅሱ ‘የይሖዋ ቃል ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል’ ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ ባይኖር ኖሮ ሕይወቴ ምን ሊመስል እንደሚችል ማሰብ እንኳ ይከብደኛል፤ ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን እስከ ዛሬ ድረስ ጠብቆ ስላቆየልን በጣም አመሰግነዋለሁ። አሁን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በራሳችን ቋንቋ በሚክስቴክ (ጉዌሬሮ) ማግኘት ችለናል።”

ሌላ ተርጓሚ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ድጋፍ እንደሰጠን አልጠራጠርም። ቋንቋ ለይሖዋ እንቅፋት እንደማይሆንበት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እርግጠኛ ሆኛለሁ። ይሖዋ ‘ቃሉ እንዳልታሰረ’ በድጋሚ አረጋግጦልናል።”—2 ጢሞቴዎስ 2:9