በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 23, 2021
ሜክሲኮ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቶሆላባል ቋንቋ ወጣ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቶሆላባል ቋንቋ ወጣ

ሐምሌ 18, 2021 የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አርቱሮ ማንዛናሬስ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቶሆላባል ቋንቋ መውጣቱን ገለጸ።

የቶሆላባል ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት ከ66,000 የሚበልጡ ቀደምት የአገሬው ተወላጆች በዋነኝነት የሚኖሩት በደቡብ ምሥራቅ ሜክሲኮ፣ በጓቴማላ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው በቺያፓስ ግዛት ነው። መጽሐፍ ቅዱሱ በዲጂታል ፎርማት መውጣቱ የተገለጸው፣ አስቀድሞ በተቀረጸ ንግግር አማካኝነት ሲሆን 2,800 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።

ተናጋሪው በፕሮግራሙ ላይ “የቶሆላባል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?” በማለት ጠይቆ ነበር። ከዚያም ምላሹን ሲሰጥ “የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ለሆነው ለይሖዋ ክብር የሚሰጥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስፈልገን ነው” አለ።

በትርጉም ሥራው የተካፈለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ዮሐንስ 5:28, 29⁠ን ሳነብ ልቤ በጥልቅ ተነካ። እናቴ ከሞት ስትነሣ በዓይነ ሕሊናዬ ታየኝ። ይህን ጥቅስ በስፓንኛ ብዙ ጊዜ አንብቤዋለሁ፤ ሆኖም አሁን በራሴ ቋንቋ ሳነበው ትርጉሙ ይበልጥ ገባኝ። በጣም አመሰግናለሁ!”

በላስ ማርጋሪታስ፣ ቺያፓስ የሚገኘው አዲሱ የቶሆላባል የርቀት የትርጉም ቢሮ

በትርጉም ሥራው ወቅት የትርጉም ቡድኑ በሜክሲኮ ሲቲ አቅራቢያ ከሚገኘው የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ በመውጣት በላስ ማርጋሪታስ፣ ቺያፓስ ወደሚገኘው አዲስ የርቀት የትርጉም ቢሮ ተዛወረ። የትርጉም ቢሮው የሚገኘው ከቅርንጫፍ ቢሮው 990 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ሲሆን በዚያ አካባቢ ቶሆላባል በስፋት ይነገራል። በአሁኑ ወቅት በርቀት የትርጉም ቢሮው ውስጥ ዘጠኝ የሙሉ ጊዜ ተርጓሚዎችና ድጋፍ ሰጪ በሆኑ ዲፓርትመንቶች ውስጥ የሚሠሩ አምስት ወንድሞች አሉ። በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቶሆላባል ተናጋሪዎች እርስ በርስ መግባባት ቢችሉም የሚጠቀሙባቸው አንዳንድ አገላለጾች ይለያያሉ። ተርጓሚዎቹ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ትክክለኛ በሆነና ለአብዛኛው ሰው በሚገባ መንገድ ለመተርጎም ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

ለምሳሌ ያህል፣ ሌሎች የቶሆላባል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “የአምላክ መንግሥት” የሚለውን አገላለጽ “አምላክ የሚገዛበት ቦታ” ወይም “የአምላክ ከተማ” በማለት ተርጉመውታል። ሆኖም የቋንቋው ተናጋሪዎች እነዚህን አገላለጾች ስለማይጠቀሙባቸው ሐሳቡ ለእነሱ ግልጽ አይደለም። በቶሆላባል የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም ለሰዎች በቀላሉ በሚገባ መንገድ “የአምላክ መንግሥት” በማለት አስቀምጦታል።

ስብሰባውን የተከታተለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ግልጽ፣ ትክክለኛና ለመረዳት ቀላል የሆነ ትርጉም እንዲያዘጋጁ በሥራው የተካፈሉትን በሙሉ እንደመራቸው ምንም ጥያቄ የለውም። ይህ ስጦታ አምላክን የማያውቁ ብዙ ሰዎች ልባቸው እንዲነካ እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነኝ።”—የሐዋርያት ሥራ 17:27