ሰኔ 23, 2021
ሜክሲኮ
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቾል ቋንቋ ወጣ
ሰኔ 20, 2021 የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሮበርት ባትኮ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቾል ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ። መጽሐፍ ቅዱሱ በዲጂታል ፎርማት መውጣቱ የተገለጸው፣ አስቀድሞ በተቀረጸ ንግግር አማካኝነት ሲሆን 800 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።
አጭር መረጃ
ቾል በዋነኝነት የሚነገረው በደቡባዊ ምሥራቅ ሜክሲኮ በሚገኘው በቺያፓስ ግዛት በሚኖሩ ቀደምት የአገሬው ተወላጆች ነው
200,000 ያህል ሰዎች የቾል ቋንቋን እንደሚናገሩ ይገመታል
የቾል ቋንቋን በሚጠቀሙ 22 ጉባኤዎችና 2 ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ ከ500 የሚበልጡ አስፋፊዎች አሉ
በሥራው የተካፈሉት 3 ተርጓሚዎች ሥራውን ለማጠናቀቅ 27 ወራት ፈጅቶባቸዋል
በትርጉም ሥራው የተካፈለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ይህ አዲስ ትርጉም የሚጠቀመው በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምንጠቀምባቸውን ቃላት ነው። እያንዳንዱን ምዕራፍ ማንበብ ያስደስተኛል።”
ሌላ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን በስፓንኛ ማንበብ እችላለሁ፤ ሆኖም በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ በቾል የተዘጋጀውን ይህን ትርጉም ሳነብ ልቤ ይነካል። የቤት ምግብ እንደመብላት ነው።”
ይህ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የቾል ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞቻችን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ‘የተሸሸገ ሀብት’ ለመፈለግ በሚያደርጉት ጥረት እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።—ምሳሌ 2:4, 5