በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 3, 2019
ሜክሲኮ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በዛፖቴክ (ኢስመስ) ቋንቋ ወጣ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በዛፖቴክ (ኢስመስ) ቋንቋ ወጣ

መስከረም 27, 2019 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በዛፖቴክ (ኢስመስ) ቋንቋ ወጣ፤ መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱ የተገለጸው በሳን ብላስ አቴምፓ፣ ኦሃካ፣ ሜክሲኮ በተካሄደ 1,983 ሰዎች የተገኙበት የክልል ስብሰባ ላይ ነበር። አዲሱ መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱን ያበሰረው የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጆኤል ኢሳጊሬ ሲሆን ወደ ዛፖቴክ (ኢስመስ) a ከተተረጎሙት መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም የያዘው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።

ተርጓሚዎቹ ይህን የትርጉም ሥራ ባከናወኑበት ወቅት ለየት ያሉ ችግሮች አጋጥመዋቸዋል። የትርጉም ቡድኑ ወደ ርቀት የትርጉም ቢሮ ከተዛወረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በአካባቢው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አለመረጋጋት ተፈጠረ። ዓማፂ ቡድኖች ወደ ከተማው የሚገቡትን መንገዶች ዘጉ። ይህ ሁኔታ ለአንድ ወር ያህል በመቆየቱ የምግብ እጥረት ተፈጥሮ ነበር። ደስ የሚለው ነገር በከተማው ዙሪያ ባሉ መንደሮች የሚኖሩ ወንድሞቻችን በእርሻቸው ላይ ያመረቱትን አትክልትና ፍራፍሬ ለተርጓሚዎቹ ይሰጧቸው ነበር። መስከረም 7, 2017 በመሬት መንቀጥቀጥ መለኪያ 8.2 የተመዘገበ የምድር መናወጥ ተከስቶ በትርጉም ቢሮው ላይ ከባድ ጉዳት ባደረሰበት ወቅት ደግሞ ተርጓሚዎቹ ሌላ እንቅፋት ገጠማቸው። የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ ተርጓሚዎቹ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው እንዲገቡ ለማድረግ አፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። በተጨማሪም አንድ የበላይ አካል አባል ከሁሉም የትርጉም ቡድኑ አባላት ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በመገናኘት ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል።

አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የዛፖቴክ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ በርካታ ሰዎች “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

a ሜክሲኮ ውስጥ የዛፖቴክ (ኢስመስ) ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ከ85,000 የሚበልጡ ሰዎች ይገኛሉ። ይህ ቋንቋ በዛፖቴክ ቋንቋ ሥር ከሚመደቡት ከ50 የሚበልጡ የተለያዩ ቀበሌኛዎች አንዱ ነው።