በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የአሁኑ የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ ከሜክሲኮ ሲቲ በስተ ምሥራቅ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል

ጥር 30, 2023
ሜክሲኮ

የይሖዋ ምሥክሮች የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ቦታ ሊቀይር ነው

የይሖዋ ምሥክሮች የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ቦታ ሊቀይር ነው

በአሁኑ ወቅት ሜክሲኮ ውስጥ በሜክሲኮ ሲቲ አቅራቢያ የሚገኘውን የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ወደ ሌላ ቦታ ለመቀየር የቀረበውን ሐሳብ የበላይ አካሉ አጽድቆታል። ይህን ሥራ እንዲያስተባብር አምስት አባላት ያሉ የግንባታ ፕሮጀክት ኮሚቴ ተቋቁሟል። በአሁኑ ወቅት ኮሚቴው፣ ቅርንጫፍ ቢሮው የሚዛወርበትን ቦታ እየፈለገ ነው።

አሁን ያለው ቅርንጫፍ ቢሮ ከ1974 አንስቶ ለበርካታ ጊዜያት የማስፋፊያና የእድሳት ሥራዎች ተደርገውለታል። በ2011 በሆንዱራስ፣ በቤሊዝ፣ በኒካራጓ፣ በኤል ሳልቫዶር፣ በኮስታ ሪካ፣ በጓቴማላ እና በፓናማ የሚከናወነው ቲኦክራሲያዊ ሥራ በማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ a ሥር እንዲሆን ተወሰነ። አሁን ካለው ሰፊ ሥራ አንጻር ቅርንጫፍ ቢሮው ተጨማሪ የማስፋፊያና የእድሳት ሥራ እንደሚያስፈልገው ታምኖበታል። በመሆኑም በማዕከላዊ ቅርንጫፍ ቢሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣውን ሥራ ግምት ውስጥ በማስገባት በሌላ ቦታ አዲስ ሕንፃ ለመገንባት ተወስኗል፤ ይህም የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ለማገዝ የሚያስችል ይበልጥ አመቺ የሥራ አካባቢ ይፈጥራል።

ቅርንጫፍ ቢሮውን የማዛወር ሥራው በተለያዩ ምዕራፎች የሚካሄድ ይሆናል። በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ የመሬት ግዢ እንዲሁም ለ300 ቤቴላውያን የሚሆኑ የመኖሪያና የሥራ ሕንፃዎችን የመገንባት ሥራ ይከናወናል። በቀጣዮቹ ምዕራፎች ደግሞ ለቤቴል ቤተሰብ የሚያስፈልጉ ቀሪ የመኖሪያና የሥራ ሕንፃዎችን ለመገንባት አቅደናል።

የግንባታ ኮሚቴው አባል የሆነው ወንድም ጆሴፍ ዪ እንዲህ ብሏል፦ “በአሁኑ ወቅት አዲሱን ቅርንጫፍ ቢሮ በየትኛው የሜክሲኮ ግዛት እንገንባ የሚለውን ለመወሰን ከማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ጋር እየተወያየን ነው። ግምት ውስጥ ከምናስገባቸው ነገሮች አንዱ በተቻለ መጠን ለፕሮጀክቱ ተባባሪ የሆኑ ባለሥልጣናትና ማኅበረሰብ ያሉበትን አካባቢ መምረጥ ነው። ይሖዋ የምናደርገውን ጥረት እንዴት እንደሚመራው ለማየት ጓጉተናል።”

አዲስ የታቀደው ይህ ቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክት በጣም አስደስቶናል፤ ይሖዋ እንዲባርከውም ጸሎታችን ነው።—ምሳሌ 16:3

a የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ እስከ 2014 ድረስ የሜክሲኮ ቅርንጫፍ ቢሮ ተብሎ ነበር የሚጠራው።