በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 23, 2022
ሞሪሸስ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በሞሪታንያኛ ክሪኦል ወጣ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በሞሪታንያኛ ክሪኦል ወጣ

የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሉዊ ብሬይን ታኅሣሥ 17, 2022 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በሞሪታንያኛ ክሪኦል ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። a ዜናው የተሰማው አስቀድሞ በተቀዳ ንግግር አማካኝነት ነው፤ ንግግሩን ከ2,200 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች ተከታትለውታል። ይህ ትርጉም በሕትመትም ሆነ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት ወጥቷል።

ሞሪታንያኛ ክሪኦል በዋነኝነት የሚነገረው ሞሪሸስ ውስጥ ነው፤ ሞሪሸስ፣ በሕንድ ውቅያኖስ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ የምትገኝ ደሴት ናት። ደሴቷ 2,007 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት አላት፤ ከማዳጋስካር በስተ ምሥራቅ 800 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ትገኛለች። ከደቡብ አፍሪካ የመጡ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህች ደሴት ላይ መስበክ የጀመሩት ገና በ1933 ነው። በ1951 የመጀመሪያው ጉባኤ ተቋቋመ፤ ስብሰባዎች የሚደረጉት በሞሪሸስ የሥራ ቋንቋ፣ በእንግሊዝኛ ነበር።

እስከ ዛሬ ድረስ በሞሪታንያኛ ክሪኦል ቋንቋ የተዘጋጀው ሙሉ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም አንድ ብቻ ነበር። ሆኖም በዚህ ትርጉም ላይ ይሖዋ የሚለው መለኮታዊ ስም አይገኝም። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ውስጥ ግን የይሖዋ ስም 237 ጊዜ ይገኛል። በተጨማሪም ይህ ትርጉም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትን የሚያስቀምጠው ለመረዳት ቀላል በሆነ ቋንቋ ነው።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ ተርጓሚዎቹ ሥራቸውን ለተወሰነ ጊዜ ለማቋረጥ ተገድደው ነበር። አንድ ተርጓሚ ሁኔታውን ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፦ “ሥራችንን ድጋሚ የቀጠልነው በከፍተኛ ቅንዓት ነው። ፕሮጀክቱ ቀድሞ ከነበረውም ይበልጥ መፍጠን ጀመረ። እንዲያውም ከወረርሽኙ በፊት ባስቀመጥነው ቀነ ገደብ መጨረስ ችለናል።”

ይህ አዲስ ትርጉም፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት እንደሚረዳቸው እርግጠኞች ነን።—ኢሳይያስ 65:13

a የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ኮሚቴ በሞሪሸስ የሚከናወነውን የስብከት ሥራ ይከታተላል