በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የሞናኮ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንፃ

ኅዳር 23, 2022
ሞናኮ

የሞናኮ የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና አገኙ

የሞናኮ የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና አገኙ

ኅዳር 19, 2022 የይሖዋ ምሥክሮች ሞናኮ ውስጥ ሕጋዊ እውቅና አግኝተዋል። ይህ ሕጋዊ እውቅና የተገኘው የሞናኮ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለይሖዋ ምሥክሮች ያስተላለፋቸውን ሁለት አዎንታዊ ብይኖችና የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።

ወንድሞቻችን ጉዳያቸውን ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት አቅርበው ነበር፤ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤቱ የሞናኮ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ጠየቀ።

በደንቡ መሠረት የአንድ አገር መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥ ሲጠየቅ በመጀመሪያ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ቡድኖች ይደራደራሉ፤ የሚያስማማቸው ውሳኔ ላይ ለመድረስም ጥረት ይደረጋል። በዚህ ሂደት የሞናኮ መንግሥት እኛን የሚጠቅም ምላሽ ሰጥቷል። ታኅሣሥ 9, 2021 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ በሞናኮ መንግሥትና በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የተደረሰውን ድርድር በይሁንታ ተቀብሎታል። በድርድሩ መሠረት የሞናኮ መንግሥት ለድርጅታችን ሕጋዊ እውቅና እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል፤ ይህም አምልኳችንን ያለምንም ገደብ ለማከናወን ያስችለናል። በተጨማሪም መንግሥት ከክሱ ጋር በተያያዘ ያወጣነውን ወጪ ለመሸፈን ተስማምቷል፤ ወጪው ከ35,000 ዩሮ (40,000 የአሜሪካ ዶላር) በላይ እንደሚሆን ይገመታል።

ኅዳር 16, 2022 መንግሥት “የሞናኮ የይሖዋ ምሥክሮች የአምልኮ ማኅበር” የተሰኘው ሕጋዊ ሰውነት በይፋ መመዝገቡን የሚያሳውቅ ሰነድ አጸደቀ። ይህ ሰነድ ኅዳር 18, 2022 በሞናኮ ብሔራዊ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቷል።

የሞናኮ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የመንግሥት ክልከላ ሳይኖርባቸው አምልኳቸውን በነፃነት ማከናወን በመቻላቸው በጣም ደስ ብሎናል። ለረጅም ጊዜ ስንጠብቅ የቆየነውን ይህን ሕጋዊ ድል ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።—ፊልጵስዩስ 1:7