በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሰኔ 22, 2023
ሞዛምቢክ

ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በቻንጋና (ሞዛምቢክ) ቋንቋ ወጣ

ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በቻንጋና (ሞዛምቢክ) ቋንቋ ወጣ

ሰኔ 18, 2023 ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በቻንጋና (ሞዛምቢክ) ቋንቋ ወጣ። የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ቻርልስ ፎንሴካ፣ በሞዛምቢክ ዋና ከተማ በማፑቶ በተደረገ ስብሰባ ላይ ለተገኙ 16,245 ታዳሚዎች የመጽሐፍ ቅዱሱን መውጣት አብስሯል። የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የታተመ ቅጂ ለተሰብሳቢዎቹ ታድሏል። በኤሌክትሮኒክ ቅጂ የተዘጋጀውንም ማውረድ ተችሏል።

ቻንጋና (ሞዛምቢክ) በዋነኝነት የሚነገረው በሞዛምቢክ ደቡባዊ ጫፍ በሚገኙት በማፑቶና በጋዛ ግዛቶች በሚኖሩ 4.2 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ነው። ቻንጋና (ሞዛምቢክ) በርካታ ቀበሌኛዎች ስላሉት የትርጉም ቡድኑ ሥራውን ሲያከናውን፣ አብዛኞቹ የቻንጋና (ሞዛምቢክ) ተናጋሪዎች የሚረዷቸውን ቃላት ለማግኘትና ለመጠቀም ጥረት አድርጓል፤ በመሆኑም በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ የቋንቋው ተናጋሪዎች ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መረዳት ይችላሉ።

የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት ብዙዎቹ አስፋፊዎች፣ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በቻንጋና (ሞዛምቢክ) ከመውጣቱ በፊት የሚጠቀሙት በጾንጋ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ነበር፤ ጾንጋ ከቻንጋና (ሞዛምቢክ) ጋር ተቀራራቢ የሆነ ቋንቋ ነው። ለአንዳንዶች ግን በጾንጋ ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መረዳት ከባድ ይሆንባቸው ነበር። አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “አሁን አዲሱ የመጽሐፍ ትርጉም ስለወጣ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የቻንጋና (ሞዛምቢክ) ተናጋሪዎችን ልብ መንካት ይችላል።”

አንድ ሌላ ተርጓሚ ደግሞ በቻንጋና (ሞዛምቢክ) የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም ይበልጥ ግልጽ እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ጠቅሷል፦ “በአካባቢው በሚነገሩ ሌሎች ቋንቋዎች በተዘጋጁ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ‘መንፈስ’ የሚለው ቃል የተተረጎመው ‘ሰው ከሞተ በኋላ ከሥጋው ተለይታ መኖሯን የምትቀጥል ነገርን’ እንደሚያመለክት በሚጠቁም የተሳሳተ መንገድ ነው። በቻንጋና (ሞዛምቢክ) የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም ግን ቃሉን የተረጎመው ትክክለኛውን ሐሳብ በሚያስተላልፍ መንገድ ነው፤ ‘የሕይወት ኃይል’ ወደሞተው ግለሰብ ሳይሆን ወደ ፈጣሪው እንደሚመለስ በሚያሳይ መንገድ ግልጽ አድርጎ አስቀምጦታል።”

ይሖዋ ‘ብርሃኑንና እውነቱን’ በመላክ ቃሉ ለቻንጋና (ሞዛምቢክ)ተናጋሪዎች ይበልጥ ግልጽ እንዲሆን በማድረጉ በጣም ተደስተናል።—መዝሙር 43:3