መጋቢት 2, 2021
ሞዛምቢክ
በሞዛምቢክ አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ ወጣ—የይሖዋ ምሥክሮች በትርጉም ሥራ ታሪክ አስመዘገቡ
አዲስ ዓለም ትርጉም በ200 ቋንቋዎች ይገኛል
የካቲት 28, 2021 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በንዳው ቋንቋ ወጣ። በአሁኑ ወቅት አዲስ ዓለም ትርጉም በሙሉ ወይም በከፊል በ200 ቋንቋዎች ይገኛል። በተጨማሪም ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከመውጣቱ አንድ ቀን በፊት ማለትም የካቲት 27 መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በሿቡ ቋንቋ ወጥቷል።
ሁለቱ መጽሐፍ ቅዱሶች በኤሌክትሮኒክ ቅጂ መውጣታቸውን፣ አስቀድሞ በተቀረጹ ንግግሮች አማካኝነት ያበሰረው የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አማሩ ቴሼራ ነው። በተጨማሪም ፕሮግራሞቹ በአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ እና በተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች አማካኝነት ተላልፈዋል። በሿቡ ቋንቋ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ማግኘት የማይችሉትን ለመጥቀም ሲባል በባለ 64 ገጽ ብሮሹር መልክም ይታተማል።
ሿቡ በዛምቤዚያ ግዛት በሚኖሩ 1.4 ሚሊዮን ሰዎች ይነገራል። በሿቡ ቋንቋ መስክ የሚያገለግሉ 492 አስፋፊዎች አሉ።
በዋናው መሥሪያ ቤት በሚገኘው የትርጉም አገልግሎት ክፍል ውስጥ የሚሠራው ወንድም ኒኮላስ አላዲስ እንዲህ ብሏል፦ “የማቴዎስ መጽሐፍ በሿቡ ቋንቋ መተርጎሙ ትልቅ እመርታ ነው። ከዚህ በፊት የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማግኘትም ሆነ መረዳት በጣም ከባድ ነበር።”
ንዳው በማዕከላዊ ሞዛምቢክ በሚኖሩ 1.1 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ይነገራል፤ ከእነዚህ መካከል 1,500 አስፋፊዎች ይገኙበታል።
የንዳው መጽሐፍ ቅዱስ ይተረጎም በነበረበት ወቅት ሦስት ከባድ አደጋዎች አጋጥመው ነበር። በ2019 ኢዳይ የተባለው አውሎ ነፋስ በሞዛምቢክ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ነበር። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ መላውን ዓለም ያናወጠው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሞዛምቢክም ብዙ ችግር አስከትሏል። ከዚያም በ2021 መጀመሪያ አካባቢ የተከሰተው ኢሎይስ የተባለው አውሎ ነፋስ በአገሪቱ ከባድ ውድመት አድርሷል። አምስት አባላትን ያቀፈው የትርጉም ቡድን እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩም ሥራውን በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ አጠናቅቋል።
የንዳው የትርጉም ቡድን አባል የሆነ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በዚያ ሁሉ ፈተና መሃል ሥራው መሳካቱ ለማመን የሚከብድ ነው። ይህ ተአምር እንደሆነ ይሰማኛል። የተከናወነው ሥራ ከእኛ አቅም በላይ ይመስል ነበር፤ ውጤቱ ግን ከጠበቅነው በላይ ነው። ለዚህ ሁሉ ሊወደስ የሚገባው ይሖዋ ነው።”
ወንድም አላዲስ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ተርጓሚዎቹን ጨምሮ የንዳው ቋንቋ ተናጋሪ ወንድሞቻችን በቅርብ ዓመታት ውስጥ በርካታ ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል፤ ይህም የትርጉም ሥራው እንዲዘገይ አድርጓል። ለመረዳት ቀላል የሆነው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ለወንድሞቻችን ትልቅ ጥቅም የሚያስገኝ ከመሆኑም ሌላ ንዳው ተናጋሪ ለሆነው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ማበረታቻና ማጽናኛ ይሰጣል።”
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን እንዲህ ብሏል፦ “በእያንዳንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ የሚካፈሉ ተርጓሚዎች በሙሉ መሥዋዕት መክፈላቸውና የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጣቸው አይቀርም። የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ የንዳው ትርጉም ቡድን ካጋጠሙት ሌሎች ፈተናዎች አንጻር ንዳው አዲስ ዓለም ትርጉም የወጣበት 200ኛ ቋንቋ መሆኑ አስደሳች ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በሞዛምቢክ ለሚኖሩ ንዳው ተናጋሪ የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች ታላቅ በረከት እንደሚሆንላቸው ጥርጥር የለውም።”
በዚህ ወረርሽኝ ወቅት እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሶች በመውጣታቸው ከወንድሞቻችን ጋር እንደሰታለን። በእርግጥም ይሖዋ ፈቃዱን እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል አንዳች ነገር የለም።—ኢሳይያስ 43:13