መጋቢት 9, 2023
ሞዛምቢክ
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን የያዘ ትርጉም በሮንጋ ቋንቋ ወጣ
መጋቢት 5, 2023 ሞዛምቢክ፣ ማፑቶ ከተማ ውስጥ በዚምፔቶ ብሔራዊ ስታዲየም ልዩ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፤ በዚህ ስብሰባ ላይ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በሮንጋ ቋንቋ መውጣቱ ተበስሯል። የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ካስትሮ ሳልቫዶ ይህን ብስራት ባሰማበት በዚህ ልዩ ፕሮግራም ላይ 3,150 ሰዎች ታድመዋል። ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ መጽሐፍ ቅዱስ የወጣበት ልዩ ፕሮግራም በአካል ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው ነው። ፕሮግራሙ ላይ በአካል ለተገኙ ሁሉ የታተሙ ቅጂዎች ተሰራጭተዋል።
ሮንጋ በትንሹ የ618,000 ሰዎች አፍ መፍቻ ቋንቋ ነው፤ ሞዛምቢክ ውስጥ በመላው የማፑቶ ክልል ይነገራል። ቀደም ብሎም በሮንጋ ቋንቋ የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ፤ ሆኖም በበርካቶቹ ትርጉሞች ላይ የሚገኘው የቃላት አጻጻፍና የንባብ ምልክቶች አሁን ላይ ለአብዛኞቹ አንባቢዎች ግልጽ አይደሉም።
አንድ ተርጓሚ አዲስ የወጣውን ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ለዚህ ዝግጅት በጣም አመስጋኝ ነኝ! ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲህ ያለ ግልጽና ለማንበብ ቀላል የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በማግኘታቸው በጣም እንደሚደሰቱ አውቃለሁ። ይሖዋ በቀጥታ ለልባችን የተናገረ ያህል እንዲሰማን የሚያደርግ ትርጉም ነው።”
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በመውጣቱ ወንድሞቻችን የተሰማቸውን ደስታ እኛም እንጋራዋለን፤ እንዲሁም ይሖዋ በሮንጋ ቋንቋ ክልል የሚከናወነውን ሥራ መባረኩን እንዲቀጥል ጸሎታችን ነው።—ሮም 12:15