በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ግንቦት 4, 2023
ሞዛምቢክ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በጊቶንጋ ቋንቋ ወጣ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በጊቶንጋ ቋንቋ ወጣ

ሚያዝያ 30, 2023 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በጊቶንጋ ቋንቋ ወጣ። በሞዛምቢክ፣ ኢንያምባኒ ግዛት በሚገኘው በማሺሺ ከተማ በተደረገ ልዩ ስብሰባ ላይ የመጽሐፍ ቅዱሱን መውጣት ያበሰረው የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዌን ሪጅዌይ ነው። በስብሰባው ላይ የተገኙት 920 ታዳሚዎች የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ተሰጥቷቸዋል። የኤሌክትሮኒክ ቅጂዎችም ተለቅቀዋል።

የጊቶንጋ ቋንቋ የሚነገረው በሞዛምቢክ፣ ኢንያምባኒ ግዛት ውስጥ ነው። የዚህ ግዛት ነዋሪዎች በእንግዳ ተቀባይነታቸውና በደግነታቸው ይታወቃሉ። ጊቶንጋ በኢንያምባኒ ግዛት ውስጥ በሚገኙት በማሺሺ፣ በሞረምቤን፣ በኦሞይኒ እና በጃንጋሞ ክልሎች የሚኖሩ 327,000 ገደማ ሰዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው።

በማሺሺ፣ ኢንያምባኒ ግዛት፣ ሞዛምቢክ የሚገኘው የጊቶንጋ የርቀት የትርጉም ቢሮ

ከዚህ ቀደም የነበሩት የጊቶንጋ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ለመረዳት ከባድ እንደነበሩ አስፋፊዎች ይናገራሉ። አዲሱ ትርጉም ግን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በቀላሉ በሚገባ መንገድ ስለሚያስቀምጠው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተደስተዋል። አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹን የሚያነጋግረው ቀላልና ለመረዳት የማይከብዱ ቃላትን ተጠቅሞ ነው። በተመሳሳይም የጊቶንጋ ቋንቋ ተናጋሪዎች ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በማግኘታቸው፣ አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ የተናገረውን ነገር መረዳት ቀላል ሆኖላቸዋል።”

ወንድም ሪጅዌይ የመጽሐፍ ቅዱሱን መውጣት ሲያበስር እንዲህ ብሏል፦ “ከአምላክ ጋር የቀረበ ወዳጅነት ለመመሥረት ከእኛ የሚጠበቅ ነገር አለ፤ እሱን በየቀኑ በጸሎት በማነጋገር ብቻ ሳንወሰን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚነግረንን ነገር በየቀኑ ማዳመጥ አለብን። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉምን ዛሬ ነገ ሳትሉ ማንበብ እንድትጀምሩና በየቀኑ እንድታነብቡት እናበረታታችኋለን።”

ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይህን መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘታቸው የደስታቸው ተካፋይ ነን፤ ይሖዋ በጊቶንጋ መስክ የሚከናወነውን ሥራ እንዲባርከውም እንጸልያለን።—ሮም 12:15