ነሐሴ 18, 2020
ሞዛምቢክ
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቻንጋና እና በማኩዋ ቋንቋዎች ወጣ
ቅዳሜ ነሐሴ 15 እና እሁድ ነሐሴ 16, 2020 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም የሞዛምቢክ ቋንቋዎች በሆኑት በቻንጋና እና በማኩዋ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት ወጣ። ከ8,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች ቻንጋናን፣ ከ1,700 የሚበልጡ አስፋፊዎች ደግሞ ማኩዋን ይናገራሉ።
የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ አሞሪም፣ አስቀድሞ በተቀረጸ ንግግር አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱሶቹ መውጣታቸውን አብስሯል፤ ፕሮግራሙ በኢንተርኔት አማካኝነት ለአስፋፊዎቹ ተሰራጭቷል። በተጨማሪም ወንድሞቻችን ፕሮግራሙን በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያና ከ30 በሚበልጡ የሬዲዮ ጣቢያዎች ለማስተላለፍ ፈቃድ አግኝተዋል።
ቻንጋና በዋነኝነት የሚነገረው በሞዛምቢክ ደቡባዊ ጫፍ በሚገኙት ሁለት ግዛቶች ውስጥ በሚኖሩ 1.9 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ነው። ቻንጋና የሞዛምቢክ ጎረቤት በሆነችው በደቡብ አፍሪካ ከሚነገረው የጾንጋ ቋንቋ ጋር በጣም ይመሳሰላል።
የማኩዋ ተናጋሪ የሆኑት ሰዎች የሚኖሩት በሞዛምቢክ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኙት ግዛቶች ውስጥ ነው። ማኩዋ 5.8 ሚሊዮን ገደማ በሚሆኑ ሰዎች የሚነገር ሲሆን ሞዛምቢክ ውስጥ በስፋት የሚሠራበት አገር በቀል ቋንቋ ነው።
ባለፉት በርካታ ዓመታት እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩ አስፋፊዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለማግኘት በጣም ይቸገሩ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ዋጋ በጣም ውድ ነበር፤ እንዲሁም አንዳንድ ባለሱቆች ለይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ለመሸጥ ፈቃደኛ አልነበሩም። አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ያላቸው ጉባኤዎች ነበሩ፤ መጽሐፍ ቅዱሱ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ተቀምጦ ንግግር የሚያቀርቡና ክፍል ያላቸው አስፋፊዎች እንዲጠቀሙበት ይደረግ ነበር።”
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በቻንጋና እና በማኩዋ በማግኘታቸው በጣም ተደስተናል። እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ ሰዎች “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” ለመርዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ እንተማመናለን።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4