በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 20, 2020
ሩማንያ

በሩማንያ የተከናወነው የእርዳታ ሥራ ወንድሞቻችንን ጠቅሟል፤ የከንቲባውንም አድናቆት አትርፏል

በሩማንያ የተከናወነው የእርዳታ ሥራ ወንድሞቻችንን ጠቅሟል፤ የከንቲባውንም አድናቆት አትርፏል

ሰኔ 2020 በትራንሲልቫኒያ፣ ሩማንያ በሚገኘው የሮድና ከተማ ከባድ ዝናብና ጎርፍ ተከስቷል። በዚህ የተነሳ የስድስት ወንድሞቻችን መኖሪያ ቤት ተጎድቷል። ሰኔ 27, 2020፣ በሮድና የሚያገለግለው የወረዳ የበላይ ተመልካች በአካባቢው ካሉ ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር በሦስት አጎራባች ጉባኤዎች ያሉ 25 ወንድሞችና እህቶች በአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ ሥራው እንዲካፈሉ ዝግጅት አድርጓል። a የሮድና ከተማ ከንቲባ ወንድሞቻችን ያከናወኑትን የእርዳታ ሥራ የተመለከቱ ሲሆን በአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ላይ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

የሮድና ከተማ የሚገኘው ብዙ ወንዞች ባሉበት ሸለቋማ አካባቢ ነው። ጎርፉ ከፍተኛ መጠን ያለው ጭቃና ፍርስራሽ እንዲከመር በማድረጉ ወደ ከተማዋ መግባት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። የአንዷ እህታችን ቤት የሚገኘው የሮድና ከንቲባና አብረዋቸው እየሠሩ የነበሩት ሰዎች ጭቃውንና ፍርስራሹን ለማጽዳት በተቸገሩበት አካባቢ ነው። ወንድሞቻችን በስፍራው ሲደርሱ የእህታችንን ቤት ለማጽዳት እንዲያመቻቸው ሲሉ በመጀመሪያ በአካባቢው የተቆለለውን ደለል አጸዱ። እንዲህ ማድረጋቸው የባለሥልጣናቱን ሥራ ቀላል አድርጎላቸዋል።

በኋላ ላይ ከንቲባው የአካባቢው የቴሌቪዥን ጣቢያ ባደረገላቸው ቃለ መጠይቅ ላይ ወንድሞቻችንን አመስግነዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “በጥልቅ የነካኝን አንድ ነገር ብናገር ደስ ይለኛል። . . . በመጀመሪያው ቀን ላይ ስንሠራ የነበረው በገልባጭ መኪናና በትራክተር እየታገዝን ነበር። ሆኖም ሥራውን መጨረስ አልቻልንም፤ ምክንያቱም አካባቢው በጣም ተጎድቶ ነበር። በቀጣዩ ቀን . . . ከ30 የሚበልጡ [ሰዎች] ረዱን፤ እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ምሽት ላይ ሥራውን መጨረስ ቻልን።” ንግግራቸውን ሲደመድሙ እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ ሰዎች ያን አካባቢ ወደነበረበት ለመመለስ ረድተውናል። ሁሉንም አመሰግናቸዋለሁ!”

ከዚህም በተጨማሪ ከንቲባው በአንድ ድረ ገጽ ላይ ለወንድሞቻችን “በላይ በሰማይ ያለው ይሖዋ ይባርካችሁ፤ ረጅም ዕድሜ፣ ጤናና ስኬትም ይስጣችሁ!” በማለት ጽፈዋል።

ከሩማንያ የተገኘው ይህ ተሞክሮ መልካም ምግባራችን በሰማይ ያለውን አባታችንን ይሖዋን እንደሚያስከብር የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ነው።—1 ጴጥሮስ 2:12

a በወረርሽኙ የተነሳ አብዛኛው የመልሶ ግንባታ ሥራ የተቋረጠ ቢሆንም እነዚህ ቤቶች ግን አስቸኳይ ጥገና ያስፈልጋቸው ነበር።