መስከረም 20, 2023
ሩማንያ
በሩማንያ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽና የቅርንጫፍ ቢሮ ማስፋፊያ ሕንፃዎች ተወሰኑ
ነሐሴ 26, 2023 በቱርዳ፣ ሩማንያ የሚገኘው የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ እንዲሁም በቡካሬስት፣ ሩማንያ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ ለማስፋፋት የተገነቡ ሦስት ሕንፃዎች ለይሖዋ አገልግሎት ተወስነዋል። የውሰና ንግግሩን ያቀረበው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌጅ ፍሊግል ሲሆን ንግግሩን በመሰብሰቢያ አዳራሹ 1,702 ሰዎች እና በቪዲዮ ኮንፈረንስ ሌሎች 14,101 ሰዎች ተከታትለውታል።
በውሰና ፕሮግራሙ ላይ በሩማንያ የተከናወኑትን የቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎች ግንባታ ታሪክ እንዲሁም እነዚህን ሕንፃዎች ለመገንባት የተደረገውን ጥረት ይሖዋ እንዴት እንደባረከው የሚገልጹ ሪፖርቶች ቀርበዋል። በተለያዩ የግንባታ ቡድኖች ውስጥ ያገለገሉ ወንድሞችና እህቶችም ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል። በቱርዳ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ግንባታ ላይ የተሳተፈችው እህት አይላ ድረጊቺ ከፕሮግራሙ በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “እነዚህ ሕንፃዎች ይሖዋን ለሚያስከብር ዓላማ ሲወሰኑ በማየቴ በጣም ተደስቻለሁ።” ዓለም አቀፍ የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኛ የሆነውና በቅርንጫፍ ቢሮው ማስፋፊያ ግንባታ ላይ የተሳተፈው ወንድም ብሩስ ዳየ ደግሞ “በዚህ የግንባታ ሥራ ላይ ለመካፈል ላገኘነው ልዩ አጋጣሚ በጣም አመስጋኞች ነን። ይሖዋን ለማይገባን ደግነቱ ከልባችን እናመሰግነዋለን!” ብሏል።
አዲስ የተገነቡት የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች፣ በአሁኑ ወቅት ለመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት እያገለገለ ያለ የመማሪያ ክፍልንና የቤቴላውያን መኖሪያዎችን ያካተቱ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በእነዚህ ሕንፃዎች ውስጥ የትርጉም ቢሮዎች፣ አንድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና የእንግዳ መቀበያ ቦታ ተካትተዋል። አዲሱ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ቤት ውስጥ 1,200 ሰዎችን ከቤት ውጪ ደግሞ 1,350 ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚመጡ ወደ 15,000 ለሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች አገልግሎት ይሰጣል።
ከውሰናው ፕሮግራም ጋር በተያያዘ በማግስቱ ማለትም ነሐሴ 27 በክሉዥ ናፖካ ከተማ በሚገኘው ስታድየም ልዩ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር። ፕሮግራሙን ለመከታተል 23,968 ሰዎች በስታዲየሙ ተገኝተዋል። ፕሮግራሙ በሃንጋሪያኛ፣ በሩማንያ ምልክት ቋንቋ፣ በሮማኒ (የሩማንያ)፣ በሩስያኛ፣ በሩሲያ ምልክት ቋንቋ፣ በእንግሊዝኛ እና በዩክሬንኛ ተተርጉሞ በሩማንያና በዩክሬን ለሚገኙ ጉባኤዎች ሁሉ ተላልፏል። በአጠቃላይ 121,411 ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።
እነዚህ ሕንፃዎች ለይሖዋ በመወሰናቸውና ለእሱ ለሚቀርበው ንጹሕ አምልኮ የሚያገለግሉ በመሆኑ በሩማንያ ከሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር አብረን ተደስተናል።—ኢሳይያስ 2:3