ሚያዝያ 21, 2020
ሩማንያ
የሩማንያኛ መጽሐፍ ቅዱስ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ወጣ
በሩማንያኛ የተዘጋጀው የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ሚያዝያ 19, 2020 በቡካሬስት፣ ሩማንያ በተካሄደ ልዩ ስብሰባ ላይ ወጣ። የሩማኒያ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጆን ብሬንካ በቀጥታ ስርጭትና በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በሩማንያና በሞልዶቫ ለሚገኙ የሩማንያኛ ቋንቋ ጉባኤዎች መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን አብስሯል። ስብሰባው ወደ ሃንጋሪያኛ፣ ወደ ሩማንያ ምልክት ቋንቋና ወደ ሮማኒ (የሩማንያ)ተተርጉሟል። ከ69,000 የሚበልጡ ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።
የመጽሐፍ ቅዱሱ የትርጉም ሥራ ከሦስት ዓመት በላይ የፈጀ ሲሆን ሁለት የትርጉም ቡድኖች በሥራው ተካፍለዋል። የተሻሻለው መጽሐፍ ቅዱስ ለመረዳት ቀላል የሆነና ተፈጥሯዊ ለዛውን የጠበቀ ቋንቋ ይጠቀማል፤ እንዲሁም የበኩረ ጽሑፉን ሐሳብ በትክክል ያስተላልፋል። አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም ዘመናዊ ቋንቋ ስለሚጠቀም ለማንበብ ቀላል ነው። . . . በመሆኑም አንባቢዎች በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ባለው ጠቃሚ ሐሳብ ልባቸው ይነካል።”
በትርጉም ሥራው የተካፈለ ሌላ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለመረዳት ቀላል ስለሆነ በየትኛውም ዕድሜ ላይ ያለ ሰው ሊያጠናው ይችላል። ይህ ትርጉም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በሙሉ ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ እንደሚረዳቸው ጥያቄ የለውም። በዘመናዊ ቋንቋ የተዘጋጀ ሕያው መጽሐፍ ነው።”
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ ወይም በከፊል በ186 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፤ ከእነዚህ መካከል በ2013 በወጣው የእንግሊዝኛ እትም ላይ ተመሥርተው ተሻሽለው የወጡ 31 ቋንቋዎችም ይገኙበታል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ከ65,000 የሚበልጡ ሩማንያኛ ቋንቋ ተናጋሪ የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ የተሻሻለ ትርጉም ሙሉ ጥቅም እንደሚያገኙ እንተማመናለን።
ይህ አስደሳች ክንውን ይሖዋ የሚወዱትንና በአንድነት የሚያገለግሉትን እንደሚባርክ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—ምሳሌ 10:22