በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ኮርኔሊዮ ሴፓን የመታሰቢያ በዓሉን ንግግር በሩማንያኛ ሲያቀርብ፤ ወንድም አንጄሎስ ካራምፕሊያስ ግሪክኛ ተናጋሪ ለሆነው እስረኛ ንግግሩን ሲያስተረጉም

ሚያዝያ 20, 2021
ሩማንያ

የ2021 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—የመታሰቢያው በዓል ንግግር በሩማንያ ላሉ እስረኞች በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተላለፈ

የ2021 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—የመታሰቢያው በዓል ንግግር በሩማንያ ላሉ እስረኞች በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተላለፈ

በሩማንያ ያሉ ወንድሞቻችን በጂላቫ ቡካሬስት እስር ቤት ካሉ እስረኞች ጋር ላለፉት 17 ዓመታት ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰት ከእስረኞች ጋር በአካል መገናኘት ተከለከለ። ሆኖም የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ መጋቢት 27, 2021 ከመከበሩ ከሁለት ሳምንት በፊት የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ስብሰባ እንዲደረግ ፈቀዱ። ወንድሞቻችን የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም በቪዲዮ ኮንፈረንስ ለማስተላለፍ የእስር ቤቱን ባለሥልጣናት አስፈቀዱ። ባለሥልጣናቱም በዚህ ሐሳብ ተስማሙ። በአጠቃላይ 21 እስረኞችና 4 ባለሥልጣናት የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም ተከታትለዋል።

ወንድም ኮርኔሊዮ ሴፓን የመታሰቢያውን በዓል ንግግር በሩማንያኛ አቀረበ። ወንድም አንጄሎስ ካራምፕሊያስ ደግሞ ስብሰባውን እየተከታተለ ለነበረ አንድ ግሪክኛ ተናጋሪ እስረኛ ንግግሩን ወደ ግሪክኛ አስተረጎመ። ከዋና ኃላፊዎቹ መካከል አንዱን ጨምሮ አራት የእስር ቤቱ ሠራተኞችም ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።

ወንድም ሴፓን እንዲህ ብሏል፦ “የመታሰቢያ በዓሉን ንግግር ማቅረብ መቻሌ ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማኛል። እስረኞቹ በትኩረት ማዳመጥና ኢየሱስ በከፈለላቸው መሥዋዕት ላይ ማሰላሰል ችለዋል።”

ወንድም ካራምፕሊያስ “ይሖዋ ለእስረኞቹ መስበክ የምንችልበትና እስረኞቹም የጌታ ራትን ማክበር የሚችሉበት አጋጣሚ በመክፈቱ በጣም ደስተኛ ነን” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ወደፊት በርካታ እስረኞች በኢንተርኔት አማካኝነት በምናደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ላይ እንደሚገኙና ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያጽናና ሐሳብ እንደሚያገኙ ተስፋ እናደርጋለን።”

የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት እስረኞቹ የመታሰቢያ በዓሉን ንግግር የሚሰሙበት አጋጣሚ እንዲያገኙ በመፍቀዳቸው በጣም ደስተኞች ነን።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4