በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መስከረም 16, 2020 ወንድም ሩስላን አልዬቭ እና ባለቤቱ ክርስቲና ፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት ቆመው

ታኅሣሥ 16, 2020
ሩሲያ

ለ18 ወራት በቁም እስር የቆየው ወንድም ሩስላን አልዬቭ ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ሊፈረድበት ይችላል

ለ18 ወራት በቁም እስር የቆየው ወንድም ሩስላን አልዬቭ ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ሊፈረድበት ይችላል

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

ታኅሣሥ 17, 2020 a በሮስቶቭ-ኦን-ዶን ከተማ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ከወንድም ሩስላን አልዬቭ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል። አቃቤ ሕጉ፣ ወንድም ሩስላን በሦስት ዓመት የገደብ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

አጭር መግለጫ

ሩስላን አልዬቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1987 (ቹኖያር፣ ክራስናያርስክ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ቤተሰቡ ብዙ ጊዜ መኖሪያ አካባቢ ይቀይር ነበር፤ አዘርባጃን እና ዩክሬን ውስጥ ኖረዋል። ግንበኛ፣ የሽያጭ አማካሪ፣ የጊታር አስተማሪ እንዲሁም የእንግሊዝኛና የቻይንኛ ቋንቋ አስተማሪ ሆኖ ሠርቷል። ስፖርታዊ ጨዋታ ያስደስተዋል፤ ግጥምና ሙዚቃም ይደርሳል። አራት ቋንቋዎች ይናገራል። ባለቤቱ ክርስቲናም ቻይንኛ ትናገራለች

    ከ13 ዓመቱ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስን ያነብና ያጠና ነበር። ይበልጥ እያጠና ሲሄድ ስለ ሕይወት የነበሩትን ጥያቄዎች በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚመልስለት ተገነዘበ። በዚህም ምክንያት ራሱን ለአምላክ ወስኖ በ2006 ተጠመቀ

የክሱ ሂደት

ሰኔ 6, 2019 በወንድም ሩስላን አልዬቭ ላይ የወንጀል ክስ ተመሠረተ፤ በዚህም የተነሳ ሰኔ 10, 2019 ታሰረ። ለ24 ሰዓት ታስሮ ከቆየ በኋላ ወንድም ሩስላን እና ሲምዮን ባይባክ የተባለ ሌላ ወንድም በቁም እስር እንዲቆዩ ተደረገ። መጀመሪያ ላይ ሩስላን በቁም እስር እንዲቆይ የተፈረደበት የጊዜ ርዝመት ስምንት ሳምንት ቢሆንም ውሳኔው ዘጠኝ ጊዜ ተራዝሟል። በመሆኑም የቁም እስረኛ ሆኖ 18 ወራት አሳልፏል። ሩስላን በቁም እስር ላይ እያለ ከጠበቃው፣ ከመርማሪው፣ ከተቆጣጣሪውና ከባለቤቱ በቀር ከማንም ጋር መገናኘት አይችልም። ኢንተርኔት መጠቀምም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት መልእክት መላክና መቀበል ተከልክሏል።

ሩስላን ከመታሰሩ በፊት፣ ይዋል ይደር እንጂ እንዲህ ዓይነት ስደት መምጣቱ እንደማይቀር ከባለቤቱ ከክርስቲና ጋር ያወሩ እንደነበር ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ መንፈሳዊ ፕሮግራም እንዲኖረን ጥረት አድርገናል። የዓመት መጻሕፍትና የወንድሞችን የሕይወት ታሪክ በማንበብ ስለ ስደት ብዙ አውቀናል። ስደት ላይ ያሉ ወንድሞቻችን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ቢሆኑም እንኳ ተስፋ እንዳልቆረጡ እንዲያውም በሁኔታው ቀልደው ለማለፍ ይሞክሩ እንደነበር አስተውለናል።” አክሎም ሩስላን “ከፊታችን የሚጠብቁንን ነገሮች ለመወጣት የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጠን ይሖዋን ጠይቀነው ነበር” ብሏል።

ሩስላን ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ ነገሮች ከሌሎች ጋር መወያየቱም ጠቅሞታል። እንዲህ ብሏል፦ “በጉባኤ ውስጥ ያሉ አስፋፊዎችን ለማበረታታት ስል ምርምር አድርጌ ነበር፤ በዚህም በርካታ የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና የሚያበረታቱ ርዕሶች አግኝቻለሁ። በኋላ ላይ ማጽናኛ ባስፈለገኝ ጊዜ የረዱኝ እነዚሁ ምርምር ሳደርግ ያገኘኋቸውና በቃሌ የያዝኳቸው ጥቅሶችና ርዕሶች ናቸው።”

ሩስላንም ሆነ ክርስቲና ለስደት በመዘጋጀታቸው ተጠቅመዋል። ቤታቸው በተፈተሸበት ወቅት የተሰማውን ሲናገር “ተረጋግቼ ነበር፤ ምንም አልተጨነቅኩም” ብሏል። በምርመራው ወቅት መርማሪው በክርስቲናም ላይ የወንጀል ክስ እንደሚመሠርቱባት ዝቶ ነበር። ሩስላን ሁኔታውን አስታውሶ እንዲህ ብሏል፦ “ውዷ ባለቤቴ ክርስቲና፣ የወንጀል ክስ ሊመሠረትባት እንደሚችል ማወቋ አላስፈራትም። ይህን ማየቴ እኔንም በጣም አበረታቶኛል፤ ኃይል ሰጥቶኛል።”

ሩስላን የቁም እስረኛ መሆኑ ለእሱም ሆነ ለክርስቲና ሕይወት ከባድ እንዲሆን አድርጓል። ሆኖም ሩስላን እንዲህ ብሏል፦ “በቁሳዊ፣ በመንፈሳዊም ሆነ በስሜት ረገድ ይሖዋ ምንጊዜም የሚያስፈልገኝን ነገር ሁሉ ያደርግልኛል፤ እኔም ከዚህ በላይ የምፈልገው ነገር የለም። እኛ በበኩላችን ገና ከረጅም ጊዜ በፊት በይሖዋ መታመንን እንዲሁም ቀላል ሕይወት በመምራት ረክቶ መኖርን ተምረናል። ይህም ካላስፈላጊ ጭንቀት ጠብቆናል።”

የሩስላን የቁም እስር ጊዜ እንዲራዘም በተወሰነበት በአንደኛው የፍርድ ሂደት ላይ ወዳጆቹ ፍርድ ቤት እንዲገቡ አልተፈቀደላቸውም ነበር። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ግን ከፍርድ ቤቱ ውጭ ቆመው ሩስላን ብቅ ሲል በጭብጨባ ተቀበሉት፤ እንዲሁም “ሩስላን፣ ከጎንህ ነን!” ብለው ጮኹ።

በሩሲያ ያሉት ወንድሞችና እህቶች የተዉትን ግሩም ምሳሌ በጣም እናደንቃለን። ስደት እየደረሰባቸው ያለው ምንም ሳያጠፉ ቢሆንም በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመናቸውን ቀጥለዋል።—መዝሙር 118:6-9

a ቀኑ ሊቀየር ይችላል