በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በሩሲያ የሚገኘው የካሉጋ ክልላዊ ፍርድ ቤት

ጥቅምት 16, 2019
ሩሲያ

ሩሲያዊው ዳኛ ከወንድም ኩዚን ክስ ጋር በተያያዘ ሕግ እንደጣሱ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ገለጸ

ሩሲያዊው ዳኛ ከወንድም ኩዚን ክስ ጋር በተያያዘ ሕግ እንደጣሱ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ገለጸ

የካሉጋ አውራጃ ፍርድ ቤት፣ ወንድም ዲሚትሪ ኩዚን ችሎት ፊት ሳይቀርብ እንዲታሰር ማድረጉ ከፍተኛ የሕግ ጥሰት መሆኑን የካሉጋ ክልላዊ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ስቬትላና አናቶልዬቭና ፕሮኮፌቫ መስከረም 9, 2019 ገልጸዋል።

እኚህ ዳኛ የይሖዋ ምሥክሮች ሩሲያ ውስጥ ፍትሐዊ የሆነ ፍርድ እየተሰጣቸው እንዳልሆነ ማመናቸው ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለ ነገር እምብዛም አያጋጥምም። ዳኛዋ የአውራጃ ፍርድ ቤቱ ከወንድም ኩዚን ክስ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ሕግ በመጣሱ ተችተውታል። የአውራጃ ፍርድ ቤቱ ወንድም ኩዚንን በሃይማኖቱ የተነሳ እንዳሾፈበትና ለክሱ መልስ እንዲሰጥ በቂ ዕድል እንዳልሰጠው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ታዝቧል። አክለውም ዳኛዋ “ችሎቱን የመሩት [የአውራጃ ፍርድ ቤቱ] ዳኛ ፍትሐዊ ነበሩ ብሎ መናገር እንደማይቻል” ገልጸዋል።

ወንድም ዲሚትሪ ኩዚንና ባለቤቱ ስቬትላና በሠርጋቸው ቀን፣ 2013

ወንድም ኩዚን የታሰረው ሰኔ 26, 2019 በካሉጋ የሚገኙ የፌዴራል ደኅንነት አገልግሎት ወታደሮች ቤቱን በበረበሩበት ወቅት ነበር። ከሁለት ቀናት በኋላ የካሉጋ አውራጃ ፍርድ ቤት፣ ወንድም ኩዚን ክሱ ከመታየቱ በፊት ለሁለት ወር እንዲታሰር ወሰነ። ነሐሴ 19 የከተማዋ የፌዴራል ደኅንነት አገልግሎት መርማሪ፣ የወንድም ኩዚን እስር ለተጨማሪ ሁለት ወራት እንዲራዘም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ፍርድ ቤቱም በጥያቄው መሠረት እስሩን አራዝሞታል።

ወንድም ኩዚን ወደ ከፍተኛው ክልላዊ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቀ ሲሆን ይግባኙን ያዩት ስቬትላና አናቶልዬቭና ፕሮኮፌቫ ነበሩ። ዳኛዋ የበታቹ ፍርድ ቤት ዳኛ ሕግ እንደተላለፉ ስለተሰማቸው የወንድም ኩዚንን ጉዳይ በበታቹ ፍርድ ቤት ያለ ሌላ ዳኛ እንዲያየው ወሰኑ። የሚያሳዝነው መስከረም 23 በአውራጃው ፍርድ ቤት ጉዳዩን ያዩት አዲሱ ዳኛም የወንድም ኩዚን እስር በሁለት ወር እንዲራዘም በይነዋል።

ፍትሐዊና ታማኝ አምላክ የሆነው ይሖዋ በሩሲያ ውስጥ በእሱ የሚተማመኑ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንደሚንከባከባቸው እርግጠኞች ነን።—ዘዳግም 32:4, 9-11