በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የፌዴራል የገንዘብ ቁጥጥር ቢሮ ዋና መሥሪያ ቤት

ጥር 13, 2023
ሩሲያ

ሩሲያ በመቶዎች በሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን መጣሏን ገፍታበታለች

ሩሲያ በመቶዎች በሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን መጣሏን ገፍታበታለች

ሩሲያ ውስጥ ገንዘብ ነክ ወንጀሎችን ለምሳሌ ጽንፈኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን ለመከላከል የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም አለ፤ ይህ ተቋም የፌዴራል የገንዘብ ቁጥጥር ቢሮ ተብሎ ይጠራል። ተቋሙ፣ በጽንፈኝነት ወይም በአሸባሪነት እንቅስቃሴ የተጠረጠሩ ስሞች የተዘረዘሩበትን መዝገብ ይከታተላል። አንድ ሰው ጥፋተኝነቱ ሕግ ፊት ባይረጋገጥም እንኳ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ሊካተት ይችላል።

የሩሲያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ እንዲታገድ በ2017 ካስተላለፈው ውሳኔ ወዲህ የ525 ወንድሞችና እህቶች ስም በዚህ መዝገብ ላይ ሰፍሯል። a ከእነዚህ መካከል ከ100 በላይ አረጋውያን የይሖዋ ምሥክሮችም ይገኙበታል።

በዚህ መዝገብ ውስጥ የተካተቱ ሰዎች ከበድ ያሉ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ይጣሉባቸዋል። ለምሳሌ ያህል የባንክ ሒሳባቸውን ማንቀሳቀስ አይችሉም፤ በየወሩ ለመላ ቤተሰባቸው ማውጣት የሚፈቀድላቸው ገንዘብ ከ10,000 ሩብል (ከ137 የአሜሪካ ዶላር) ገደማ አይበልጥም። የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን አዳጋች ወይም እጅግ አስቸጋሪ የሚያደርጉባቸው ሌሎች ክልከላዎችም ተጥለውባቸዋል። ለምሳሌ ቤት ወይም መኪና ለመግዛትና ለመሸጥ፣ ኢንሹራንስ ለመግባት፣ ሥራ አልባ ለሆኑ ሰዎች የሚሰጠውን ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት፣ ውርስ ለመቀበል እንዲሁም ከባንክ ለመበደር ብዙ ተግዳሮቶች አሉባቸው። ጡረተኛ ወይም የአካል ጉዳተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ ይበልጥ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ናቸው፤ ምክንያቱም የሕክምና ወጪያቸውን መሸፈን ይቸገራሉ፤ በሕዝብ ትራንስፖርት ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ዝግጅትም ተነጥቀዋል።

በኡሱሪስክ የሚኖረውና ታኅሣሥ 2019 በዚህ መዝገብ ውስጥ የተካተተው ወንድም አንቶን ቼርምኒክ እንዲህ ብሏል፦ “ደሞዜን ለመቀበል፣ በየወሩ እየሄድኩ ገንዘቡን ያገኘሁት በወንጀል እንዳልሆነ ማስመሥከር ይጠበቅብኛል። ብዙ ሰነድ ይዤ ነው የምሄደው፤ የባንኩ ሠራተኞች ሰነዶቹን ኮፒ ካደረጉ በኋላ ወደ ሞስኮ ይልኳቸዋል። የሰነድ ምርመራው ሁለት ሳምንት ይፈጃል። በቀጠሮው ቀን ወደ ባንክ እሄድና ደሞዜን ከባንክ ሒሳቤ አውጥተው ይሰጡኛል፤ ከዚያም ወዲያውኑ አካውንቴን ያግዱታል። አዲስ የባንክ ሠራተኞች ደግሞ በአሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ ስሜ እንዳለ ሲያዩ ይፈሩኛል።”

እነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አዎንታዊ አመለካከት ይዘው ቀጥለዋል። ወንድም ዩሪ ቤሎስሉድትስዬቭ የስድስት ዓመት የገደብ እስራት ፍርዱን ከመስማቱ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ስሙ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ተካትቶ ነበር፤ እንዲህ ብሏል፦ “የባንክ ሒሳቤ እንዳይንቀሳቀስ ታገደ። ሆኖም ወንድሞችና እህቶች እኔንና ባለቤቴን ረድተውናል። ላደረጉልን ድጋፍ ይሖዋን በጣም እናመሰግነዋለን።”

ይሖዋ በሩሲያ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ግፍ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ እርግጠኞች ነን። መከራቸው ባያበቃም ይሖዋ በሚያስፈልጋቸው ሁሉ እነሱን መንከባከቡን እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት አለን።—ማቴዎስ 6:33

a እስከ ታኅሣሥ 2022 ድረስ 35 ወንድሞችና እህቶች ብይናቸውን በመጨረሳቸው ወይም የገንዘብ መቀጮ በመክፈላቸው ስማቸው ከመዝገቡ ላይ ተሰርዟል