በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ዲሚትሪ ሚኻይሎቭ በቅርቡ የተደረገለት ቃለ መጠይቅ። የሩሲያ ባለሥልጣናት ግንቦት 29, 2018 ያሰሩት ሲሆን 171 ቀናት በእስር አሳልፏል

ሰኔ 18, 2019
ሩሲያ

ሩሲያ ወንድም ሚኻይሎቭን ማሰሯ ሕገ ወጥ እንደሆነ የተ.መ.ድ. የሕግ ባለሙያዎች ገለጹ

ሩሲያ ወንድም ሚኻይሎቭን ማሰሯ ሕገ ወጥ እንደሆነ የተ.መ.ድ. የሕግ ባለሙያዎች ገለጹ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) ሥር ያለ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ የሕግ ባለሙያዎች ያቀፈ ቡድን ሩሲያ ወንድም ዲሚትሪ ሚኻይሎቭን ማሰሯ “ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ አድልዎ” ስለሆነ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እንደሚጥስ ገለጸ። በተጨማሪም ቡድኑ ሩሲያ በእሱ ላይ የመሠረተችውን የወንጀል ክሶች በሙሉ እንድታቋርጥ አጥብቆ ጠይቋል።

ዎርኪንግ ግሩፕ ኦን አርቢትራሪ ዲቴንሽን (አግባብ ያልሆነ እስራት አጣሪ ቡድን) የተባለው ቡድን ያዘጋጀው የ12 ገጽ ሰነድ ወንድም ሚኻይሎቭ ‘ሰላማዊ ያልሆነ ድርጊት ፈጽሞ እንደማያውቅ’ ገልጿል። በተጨማሪም “እሱም ሆነ በሩሲያ የሚገኙ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ዓመፅ እንዳነሳሱ ወይም ሌሎችን እንዳሳመፁ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም” በማለት ገልጿል።

አግባብ ያልሆነ እስራት አጣሪ ቡድኑ ወንድም ሚኻይሎቭ “የሃይማኖት ነፃነቱን ከመጠቀም ውጪ ምንም አላደረገም” እንዲሁም “ያለፍርድ ታስሮ መቆየት አልነበረበትም” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። በመሆኑም በእስር ቤት ቆይታው ምክንያት ሥራ መሥራት ባለመቻሉና ወንጀል ባይፈጽምም ለእስራት በመዳረጉ መንግሥት ካሳ ሊከፍለው እንደሚገባ አጣሪ ቡድኑ ገልጿል።

አጣሪ ቡድኑ፣ በእምነቱ ምክንያት ኢፍትሐዊ ድርጊት የተፈጸመው በወንድም ሚኻይሎቭ ላይ ብቻ እንዳልሆነም ተናግሯል። ቡድኑ እንዲህ ብሏል፦ “የሃይማኖት ነፃነታቸውን በመጠቀማቸው ምክንያት ብቻ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት፣ ከታሰሩትና ወንጀለኛ ተብለው ከተፈረደባቸው በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ወንድም ሚኻይሎቭ አንዱ ብቻ ነው።” የሃይማኖት ነፃነት ደግሞ በዓለም ዙሪያ ሕጋዊ ከለላ ያለው መብት ነው። በመሆኑም አጣሪ ቡድኑ በሩሲያ በሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ስደት ያወገዘ ከመሆኑም ሌላ የተላለፈው ውሳኔ የሚመለከተው ወንድም ሚኻይሎቭን ብቻ ሳይሆን “በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን” የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል።

ወንድም ሚኻይሎቭ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረው በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለ ነበር፤ ከዚያም በ1993 በ16 ዓመቱ ተጠመቀ። በ2003 የሌና ከምትባል እህት ጋር ትዳር የመሠረተ ሲሆን አብረው ይሖዋን ያገለግሉ ነበር።

በ2018 ወንድም ሚኻይሎቭና ባለቤቱ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለበርካታ ወራት ስልካቸውን ጠልፈውት እንደነበረና የሚያደርጉትንም በካሜራ ይከታተሉ እንደነበር አወቁ። በሚያዚያ 19, 2018 የሩሲያ ፌዴሬሽን የኢቫኖቮ ከልል ወንጀል ምርመራ ኮሚቴ በወንድም ሚኻይሎቭ ላይ የወንጀል ክስ በመመሥረት መሣሪያ የታጠቁ ፖሊሶች ቤቱን እንዲፈትሹ አደረገ። ከአንድ ከወር ገደማ በኋላ ወንድም ሚኻይሎቭ “ለጽንፈኞች” የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ወንጀል ተከስሶ እስር ቤት ገባ። ያለፍርድ ለስድስት ወር ገደማ (171 ቀናት) ከታሰረ በኋላ ተፈታ። ያም ሆኖ ባለሥልጣናቱ የወንጀል ምርመራውን እስኪዘጉ ድረስ የሚያደርገውን የመረጃ ልውውጥ በሙሉ የሚቆጣጠሩ ከመሆኑም ሌላ ጉዞ እንዳያደርግ ገደብ ጥለውበታል።

የሩሲያ መንግሥት በወንድም ሚኻይሎቭ ላይ ከተሰነዘረው ክስ ጋር በተያያዘ አጣሪ ቡድኑ ላስተላለፈው ውሳኔ የሰጠውን ምላሽ ይኸውም በእሱ ላይ የተመሠረተው ክስ መዘጋቱን፣ ተገቢው ካሳ መከፈሉን እንዲሁም በወንድም ሚኻይሎቭ ላይ የተፈጸመውን ኢፍትሐዊ ድርጊት በተመለከተ አስፈላጊው ምርመራ መካሄዱን በስድስት ወር ውስጥ ለአጣሪ ቡድኑ ማሳወቅ ይጠበቅበታል።

ይህ አጣሪ ቡድን ቀደም ሲል ያስተላለፈው ተመሳሳይ ውሳኔ ካዛክስታን ውስጥ ታስሮ ከነበረው ወንድም ቴይሙር አኽሜዶቭ ጋር በተያያዘም ውጤት አስገኝቶ የነበረ ይመስላል። ወንድም አኽሜዶቭ ስለ እምነቱ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመስበኩ የተነሳ በ2017 ታስሮ የነበረ ሲሆን የአምስት ዓመት እስራት ተፈርዶበት ነበር። የወንድም አኽሜዶቭ ጠበቆች በአገሪቱ ውስጥ ባሉት ፍርድ ቤቶች በሙሉ መፍትሔ ማግኘት ባለመቻላቸው አቤቱታቸውን ለአጣሪ ቡድኑ አቀረቡ። አጣሪ ቡድኑ ጥቅምት 2, 2017 ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ የካዛክስታን ባለሥልጣናት የፈጸሙትን ድርጊት ያወገዘ ከመሆኑም ሌላ ወንድም አኽሜዶቭ ከእስር እንዲፈታ ጠየቀ። ከስድስት ወራት በኋላ የካዛክስታን ፕሬዚዳንት ወንድም አኽሜዶቭን ከክሶቹ ነፃ አደረጉት። ወንድም አኽሜዶቭ ሚያዝያ 4, 2018 ከእስር ተፈታ።

የሩሲያ መንግሥት ከወንድም ሚኻይሎቭ ክስ ጋር በተያያዘ አጣሪ ቡድኑ ያደረገውን ውሳኔ ተቀበለም አልተቀበለ “[ይሖዋን] መጠጊያ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ እንተማመናለን። ይሖዋ በሩሲያ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው እንግልት እየደረሰባቸው ያሉትን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን መንከባከቡን እንዲቀጥል እንጸልያለን፤ እነሱም በይሖዋ ታምነው በድፍረት የሚጸኑ ሰዎች ‘መልካም ነገር እንደማይጎድልባቸው’ ማየት ይችላሉ።—መዝሙር 34:8, 10