በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ቭላዲሚር ኮክሎቭ፣ እህት ታትያና ሻምሼቫ፣ እህት ኦልጋ ሲላዬቫ እና ወንድም ኤዱዋርድ ዢንዢኮቭ

መስከረም 3, 2020
ሩሲያ

ሩሲያ ውስጥ ሁለት ወንድሞች እና ሁለት እህቶች በእምነታቸው ምክንያት ተፈረደባቸው

ሩሲያ ውስጥ ሁለት ወንድሞች እና ሁለት እህቶች በእምነታቸው ምክንያት ተፈረደባቸው

ብይን

በብሪያንስክ ክልል የሚገኘው የኖቮዚብኮቭ ከተማ ፍርድ ቤት መስከረም 3, 2020 ወንድም ቭላዲሚር ኮክሎቭ፣ እህት ታትያና ሻምሼቫ፣ እህት ኦልጋ ሲላዬቫ እና ወንድም ኤዱዋርድ ዢንዢኮቭ ጥፋተኛ እንደሆኑ በመግለጽ ፈርዶባቸዋል። ከአንድ ዓመት አንስቶ እስከ አንድ ዓመት ከሦስት ወር የሚያህል እስር ተፈርዶባቸዋል። ይሁንና ከፍርድ በፊት ታስረው በመቆየታቸው ሁሉም ተለቀዋል።

አጭር መግለጫ

ቭላዲሚር ኮክሎቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1977 (ኖቮዚብኮቭ፣ ብሪያንስክ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በሜካኒክነት ሙያ የተሰማራ። የይሖዋ ምሥክር ከመሆኑ በፊት ወታደር ነበር። እግር ኳስ ጨዋታ፣ ማንበብ፣ ዓሣ ማጥመድና ጊታር መጫወት ያስደስተዋል

  • መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ያበረታታው ጓደኛው ነው። በ2007 ከኦልጋ ጋር ትዳር መሠረተ። አነስቴዥያ የምትባል ልጅ አለቻቸው። ቤተሰቡ ይሖዋን በአንድነት ያገለግላል

ታትያና ሻምሼቫ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1977 (ቼሬፖቬትስ፣ ቮሎግዳ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ። ለበርካታ ዓመታት ኢኮኖሚክስ፣ ሕግ እና አካውንቲንግ አስተምራለች። በ1995 ተጠመቀች። ጥበብ የሚንጸባረቅበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለሌሎች ማስተማር ያስደስታታል

ኦልጋ ሲላዬቫ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1988 (ዳቪዶቮ፣ ሞስኮ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ከሦስት ልጆች መካከል የመጨረሻዋ ነች። ከአንድ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት በቴርማል ኢንጅነሪንግ በዲግሪ ተመርቃለች። እጅ ሥራ ትወዳለች። ማንበብና መረብ ኳስ መጫወት ያስደስታታል። የእናቷን ምሳሌ በመከተል የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ተቀብላለች

ኤዱዋርድ ዢንዢኮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1971 (ዛድንያ፣ ብሪያንስክ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በብየዳና በጽዳት ሥራ ተሰማርቶ የነበረ ሲሆን ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ሠርቷል። የሙዚቃ ባንድ አባል ነበር። አብራው በባንዱ ውስጥ ትጫወት ከነበረችው ከታትያና ጋር በ1993 ትዳር መሠረተ። ግጥም መጻፍና ጊታር መጫወት ይወዳል

  • በ1990ዎቹ መገባደጃ አካባቢ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመረ በኋላ ለበርካታ ጥያቄዎቹ መልስ አገኘ። ይህም ከመጥፎ ልማዶቹ ለመላቀቅና የቤተሰብ ሕይወቱን ለማሻሻል አነሳሳው። ታትያናም ይህን ስታይ ትኩረቷ ተሳበ። ስለዚህ እሷም የይሖዋ ምሥክር ሆነች

የክሱ ሂደት

ሰኔ 11, 2019 ፖሊሶች ሩሲያ ውስጥ በብሪያንስክ ክልል የሚገኙ 22 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶችን በረበሩ። እህት ታትያና ሻምሼቫ እና እህት ኦልጋ ሲላዬቫም ታሰሩ። ሁለቱም ከፍርድ በፊት ለ245 ቀናት በእስር ቆይተዋል። ግንቦት 2020 ከተፈቱ በኋላ ቤታቸው ሆነው ፍርዳቸውን እንዲጠባበቁ ተደረገ።

ጥቅምት 16, 2019 ፖሊሶች በወንድም ቭላዲሚር ኮክሎቭ እና በወንድም ኤዱዋርድ ዢንዢኮቭ ላይ ክስ መሠረቱ። ከጊዜ በኋላ ጉዳያቸው ከእህት ሻምሼቫ እና ከእህት ሲላዬቫ ክስ ጋር አብሮ እንዲታይ ተወሰነ። ከሰባት ቀናት በኋላ እነዚህ ወንድሞች ፍርድ ቤት እስኪቀርቡ ድረስ እንዲታሰሩ ተወሰነ፤ እስካሁንም እስር ቤት ነበሩ።

እህቶች በ2020 የበላይ አካሉ ሪፖርት ቁጥር 5 ላይ ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸው ነበር። እህት ሲላዬቫ ከፍርድ በፊት በእስር የቆየችበት ስምንት ወር “ሁኔታዎች ምንም ያህል ከባድ ቢሆኑ ይሖዋ ማንኛውንም ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት” እንደሚሰጠን ይበልጥ እንድትተማመን እንደረዳት ተናግራለች። እህት ሻምሼቫም “ይሖዋ ሁሌም ከጎናችን ነው፤ ምንጊዜም ይደግፈናል፤ ያጠነክረናል እንዲሁም ይረዳናል” በማለት በእርግጠኝነት ተናግራለች።

ሩሲያ ውስጥ እስር የሚጠብቃቸውም ሆኑ በአሁኑ ወቅት በእስር ያሉት ወንድሞችና እህቶች ደስታቸውንና ሰላማቸውን ሳያጡ የሚያጋጥማቸውን ፈተና እንዲወጡ ይሖዋ እንደሚረዳቸው እርግጠኞች ነን።—1 ቆሮንቶስ 10:13