በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሰርጌ ፖልያኮቭ እና እህት አነስቴዥያ ፖልያኮቫ (በስተ ግራ)፣ እህት ጋውካር ቤክቴሚሮቫ (ከላይ በስተ ቀኝ) እና እህት ዲናራ ዲዩስኬየቫ (ከታች በስተ ቀኝ)

መስከረም 25, 2020
ሩሲያ

ሩሲያ ውስጥ ሳይፈረድባቸው የታሰሩት የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እንዲሁም ሌሎች ሁለት እህቶች ሊፈረድባቸው ይችላል

ሩሲያ ውስጥ ሳይፈረድባቸው የታሰሩት የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እንዲሁም ሌሎች ሁለት እህቶች ሊፈረድባቸው ይችላል

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

በኦምስክ ከተማ የሚገኘው የፐርቮማይስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት በወንድም ሰርጌ ፖልያኮቭና በባለቤቱ አነስቴዥያ እንዲሁም በእህት ጋውካር ቤክቴሚሮቫ እና በእህት ዲናራ ዲዩስኬየቫ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ለጥቅምት 21, 2020 a ቀጠሮ ይዟል። አቃቤ ሕጉ በወንድም ሰርጌ ፖልያኮቭ ላይ የስድስት ዓመት ተኩል እስር እንዲፈረድበት ጠይቋል። ሦስቱ እህቶች ደግሞ የሁለት ዓመት እስራት በገደብ ይጠብቃቸዋል።

አጭር መግለጫ

ሰርጌ ፖልያኮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1972 (ሙርማንስክ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ኮሌጅ ተምሮ ሬዲዮፊዚዚስት ሆነ። በ2003 ከአነስቴዥያ ጋር ትዳር መሠረተ

አነስቴዥያ ፖልያኮቫ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1984 (ሙርማንስክ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ኮሌጅ ገብታ ሕግ አጥንታለች። እሷና ሰርጌ ቋንቋ መማር ያስደስታቸዋል፤ ቻይንኛ፣ ካዛክ፣ የሩሲያ ምልክት ቋንቋ እና ሰርቢያኛ ተምረዋል

ጋውካር ቤክቴሚሮቫ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1976 (ኡሪል፣ ካዛክስታን)

  • ግለ ታሪክ፦ ከስድስት ልጆች መካከል ትንሿ ነች። ያደገችው በካዛክስታን በሚገኝ ተራራማ አካባቢ ሲሆን ከልጅነቷ ጀምሮ ተፈጥሮን ታደንቃለች። ለበርካታ ዓመታት የሕይወትን ዓላማ ለማወቅ ትፈልግ ነበር። በኋላም ምክንያታዊና አርኪ የሆነ መልስ ከመጽሐፍ ቅዱስ አገኘች። የአምላክን ቃል በጥልቀት ማጥናቷ ኢፍትሐዊ የሆነ እስራት ሲያጋጥማት ለመጽናት ረድቷታል

ዲናራ ዲዩስኬየቫ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1982 (ሌኒንግራድስኮቭ፣ ካዛክስታን)

  • ግለ ታሪክ፦ በልጅነቷ ስለ ሕይወት ዓላማ በጥልቀት ታስብ ነበር። በ17 ዓመቷ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት መልእክት በመማሯ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነው አምላክ ስሙ ይሖዋ መሆኑን በማወቋ በጣም ተደሰተች። ቅርጫት ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ ሩጫና ብስክሌት መንዳት ያስደስታታል

የክሱ ሂደት

ሐምሌ 4, 2018 ሌሊት ወንድም ሰርጌ ፖልያኮቭና ባለቤቱ አነስቴዥያ ተኝተው ሳሉ ፖሊሶች የቤታቸውን በር ሰብረው ገቡ። ጭምብል ያጠለቁ ፖሊሶች ወንድም ሰርጌ ፖልያኮቭን በጭካኔ ደበደቡት። ከዚያም ፖሊሶቹ ባልና ሚስቱን ይዘው ያለፍርድ አሰሯቸው። በ2017 የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ እንዲታገድ የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ የታሰሩት የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እነሱ ናቸው። ወንድም ሰርጌ ፖልያኮቭና ባለቤቱ ለአምስት ወር ያህል እርስ በርስም ሆነ ከሌላ ሰው እንዳይገናኙ ተደርገው ለየብቻቸው ታሰሩ። ከዚያም ለሦስት ወር አብረው በቁም እስር ቆዩ።

ግንቦት 2019 ፖሊሶች በኦምስክ ክልል የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መፈተሻቸውን እንደ አዲስ ተያያዙት። በዚህም ምክንያት እህት ጋውካር ቤክቴሚሮቫ እና እህት ዲናራ ዲዩስኬየቫ ታሰሩ። ከዚያም ጉዳያቸው ከነወንድም ሰርጌ ፖልያኮቭ ክስ ጋር አብሮ እንዲታይ ተደረገ። የፍርድ ሂደቱ ሚያዝያ 1, 2020 ጀመረ።

አምላካችን ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚደርስባቸውን በደል ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጣቸው እንተማመናለን።—ኤፌሶን 3:20

a ቀኑ ሊቀየር ይችላል