በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በሩሲያ ያሉ ሁለት ወንድሞች፣ ታማኝ ቤተሰቦቻቸው ስለተዉት ምሳሌ ያስባሉ። በስተ ግራ (ከላይ)፦ ወንድም ኦሌግ ዳኒሎቭ። በስተ ግራ (ከታች)፦ የኦሌግ አያቶች የሆኑት ወንድም ፍዮዶር እና ባለቤቱ እህት የካተሪና። በስተ ቀኝ (ከላይ)፦ ቭላድሚር ዬርሞሌቭ። በስተ ቀኝ (ከታች)፦ የቭላድሚር አያቶች የሆኑት ወንድም ቫለንቲን እና ባለቤቱ እህት አና እንዲሁም የቭላድሚር አባት በትንሽነቱ።

ኅዳር 15, 2021
ሩሲያ

ሩሲያ ውስጥ ስደት እየደረሰባቸው ያሉ ወንድሞች የቀድሞ የእምነት ምሳሌዎችን ማሰባቸው አጠናክሯቸዋል

ሩሲያ ውስጥ ስደት እየደረሰባቸው ያሉ ወንድሞች የቀድሞ የእምነት ምሳሌዎችን ማሰባቸው አጠናክሯቸዋል

ሩሲያ ውስጥ ስደትን በጽናት እየተቋቋሙ ካሉት በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ወንድም ኦሌግ ዳኒሎቭ እና ወንድም ቭላድሚር ዬርሞሌቭ ይገኙበታል። እነዚህ ሁለት ደፋር ወንድሞች፣ መንፈሳዊ ውርሻቸው ብርታት እንደሰጣቸው ተናግረዋል፤ ከቤተሰቦቻቸው ያገኙት መንፈሳዊ ውርሻ፣ ድንቅ የድፍረትና የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ያካትታል።

ኦሌግ ዳኒሎቭ

የኦሌግ አያቶች የሆኑት ፍዮዶር እና የካተሪና የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት በ1958 ነው። የአገሩ መንግሥት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ በቀሰቀሰው ስደት የተነሳ የሩሲያ ባለሥልጣናት የእነዚህን ባልና ሚስት ቤት ፈትሸዋል፤ ንብረታቸውን ወስደውባቸዋል፤ እንዲሁም ፍዮዶር የገንዘብ መቀጮ እንዲከፍል አድርገዋል። ፍዮዶር ግን በዚህ ሳይረበሽ ቤተሰቡ መንፈሳዊ ልማዱን ይዞ እንዲቀጥል አድርጓል።

ፍዮዶር እና የካተሪና፣ አልፍሬድ እና ኤላ (የኦሌግ እናት) የተባሉ ልጆች አሏቸው፤ እነዚህ ልጆችም እያደጉ ሲሄዱ ፌዝና ስደት ደርሶባቸዋል። እነሱም ቢሆኑ በእምነት ጸንተዋል። በኋላ ላይ አልፍሬድ ለውትድርና ተመለመለ፤ ሆኖም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሦስት ዓመት ታስሯል።

ኦሌግ ዳኒሎቭም እንደ አጎቱ አልፍሬድ ሁሉ በእምነቱ ምክንያት የሦስት ዓመት እስራት ተፈርዶበታል። ከመጋቢት 2021 አንስቶ እስር ቤት ስለገባ ከባለቤቱ ከናታሊያ እንዲሁም ኢልያ እና ኒኪታ ከተባሉ ወንዶች ልጆቻቸው ለመለየት ተገድዷል። ቤተሰቡ፣ ይሖዋ የኦሌግን አያቶችና አጎት እንደረዳቸው ሁሉ እነሱንም እንደሚረዳቸው እምነት አላቸው።

ወንድም ኦሌግ ዳኒሎቭ እና ባለቤቱ ናታሊያ ከልጆቻቸው ከኒኪታ (በስተ ግራ) እና ከኢልያ ጋር (በስተ ቀኝ)

ኦሌግ እንዲህ ብሏል፦ “በሶቪየት ኅብረት ዘመን የነበሩ የቤተሰቤ አባላት እንዲሁም ሌሎች ወንድሞችና እህቶች መጽናት ብቻ ሳይሆን ደስታቸውን እንዴት እንደጠበቁም ብዙ ጊዜ አስባለሁ።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “እንደኔ እንደኔ፣ ይህ የይሖዋ መንፈስ ያለውን ኃይል የሚያሳይ የማያሻማ ማስረጃ ነው። እኔና ቤተሰቤም መጽናት ብቻ ሳይሆን ደስታችንን ጠብቀን መቀጠል እንደምንችልም እርግጠኛ ነኝ።”

ቭላድሚር ዬርሞሌቭ

ወንድም ቭላድሚር ዬርሞሌቭ እና ባለቤቱ ቫለሪያ

የቭላድሚር አያት የሆነችው አና ዬርሞሌቫ፣ በኢርኩትስክ ክልል በምትገኘው የሴሬብሮቮ መንደር ትኖር ነበር፤ በ1953 እውነትን ሰማች። ከመንደሯ ነዋሪዎች መካከል ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው የመጀመሪያዋ ሰው እሷ ናት። አና ከጎረቤቶቿ ከባድ ተቃውሞ ይደርስባት ነበር፤ የገዛ እናቷ እንኳ ከዚያ በኋላ አላናገረቻትም።

ባለሥልጣናቱ፣ አና እንደምትሰብክ ሲያውቁ ለልጇ ጠንቅ እንደሆነች በመግለጽ ከሰሷት፤ ቭላድሚር የተባለውን ልጇን እንደሚወስዱባት ዛቱባት።

በአና ጉባኤ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች፣ አና ጥሩ እናት እንደሆነች የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፉ። አንድ ወንድም ይህን ደብዳቤ ይዞ ወደ ሞስኮ ሄደና በወቅቱ መሪ ለነበሩት ለኒኪታ ክሩሽቼቭ ሰጣቸው። የሚገርመው፣ ክሩሽቼቭ ጉዳዩ እንዲጣራ መመሪያ ሰጡ። አና ከክስ ነፃ ስለተደረገች ባለሥልጣናቱ ልጇን አልወሰዱባትም።

አና፣ ናዴዥዳ የተባለች ሴት ልጅም ነበረቻት። ናዴዥዳ በ1970 ከባድ የሆድ ሕመም አጋጥሟት ሆስፒታል ገባች። ሐኪሞቹ፣ የሕመሙን መንስኤ በቅጡ ሳያጣሩ ኦፕራሲዮን አደረጓት። ተጣድፈው ቀዶ ሕክምና አድርገው ሲያበቁ ደም ካልወሰደች ብለው የግድ አሉ። እናትና ልጅ አቋማቸውን ለማላላት ፈቃደኞች አልሆኑም። ሐኪሞቹ ግን የእነሱን ፈቃድ ችላ በማለት ከሰውነቷ ጋር የማይስማማ ደም ሰጧት። የሚያሳዝነው፣ ከትንሽ ጊዜ በኋላ አረፈች። ይህን ስህተታቸውን ለመደበቅ የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ በስፋት በሚሰራጭ አንድ ጋዜጣ ላይ አና “ልጇን እንደሠዋች” በመግለጽ በሐሰት ወነጀሏት።

ይህ አሳዛኝ ክስተት በአና ባል በቫለንቲን ላይ ያልተጠበቀ ውጤት አምጥቷል። አና ለልጆቻቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንድታስተምር ቢፈቅድላትም እሱ ግን በዚህ አይመራም ነበር። የአና የእምነት አጋሮች በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ለቤተሰቡ ያደረጉትን ድጋፍ ሲያይ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ወሰነ፤ በኋላም የይሖዋ ምሥክር ሆነ።

ወንድም ቭላድሚር ዬርሞሌቭ እና ባለቤቱ ሊዩቦቭ

አና እና ቫለንቲን፣ ወንድ ልጃቸው ቭላድሚር በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲመራ ማሠልጠናቸውን ቀጠሉ። ቭላድሚር አደገና ሊዩቦቭ የተባለች ታማኝ እህት አገባ። እነዚህ ባልና ሚስትም በተራቸው፣ ቭላድሚር የተባለው ልጃቸው ለመንፈሳዊ ነገሮች ጥልቅ አድናቆት እንዲኖረው አድርገው አሳድገውታል።

የካቲት 2020 ፖሊሶች የቭላድሚርን እና የቫለሪያን ቤት በረበሩ። ቭላድሚር በቁጥጥር ሥር ውሎ ማረፊያ ቤት ገባ፤ በኋላም ለሁለት ወራት ገደማ የቁም እስረኛ ሆኖ ቆይቷል። እገዳ የተጣለበትን ድርጅት እንቅስቃሴ ደግፈሃል በሚል ተወንጅሎ በአሁኑ ወቅት ፍርዱን እየተጠባበቀ ነው። ጥፋተኛ ነህ ከተባለ እስከ 15 ዓመት እስራት ሊፈረድበት ይችላል። ቭላድሚር፣ ሊተላለፍበት በሚችለው ፍርድ ላይ ከማተኮር ይልቅ ወላጆቹና አያቶቹ በተዉት የታማኝነት ምሳሌ ላይ ያሰላስላል።

ቭላድሚር እንዲህ ብሏል፦ “ለአባታችን ስም ስንል መከራ መቀበል ትልቅ መብት ነው። ወላጆቼና አያቶቼ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናትና በታማኝነት ተወጥተዋል። እኔም ይህን ለማድረግ ዝግጁ ነኝ።”

እንደ ኦሌግ እና ቭላድሚር ሁሉ በሩሲያ ያሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ታማኝ ቤተሰቦቻቸው ያወረሷቸውን መንፈሳዊ ውርሻ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። እኛም በቀደመው ጊዜም ሆነ አሁን ስደትን በጽናት በመቋቋም ምሳሌ የሚሆኑ ክርስቲያኖች በተዉት አርዓያ ላይ እናሰላስል፤ ‘በእምነታቸውም እንምሰላቸው።’—ዕብራውያን 13:7