በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ኢጎር ኢቫሺን

መጋቢት 27, 2020
ሩሲያ

ሩሲያ ውስጥ በወንድም ኢጎር ኢቫሺን ላይ የሰባት ዓመት እስር ሊፈረድበት ይችላል

ሩሲያ ውስጥ በወንድም ኢጎር ኢቫሺን ላይ የሰባት ዓመት እስር ሊፈረድበት ይችላል

በሳኻ ሪፑብሊክ የሚገኘው የሌንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት የወንድም ኢጎር ኢቫሺንን ጉዳይ ተመልክቶ መጋቢት 31, 2020 ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል። አቃቤ ሕጉ በወንድም ኢጎር ላይ የሰባት ዓመት እስር እንዲበየንበት ጠይቋል።

የካቲት 2018 ፖሊሶች የወንድም ኢጎርን ስልክ እንዲጠልፉ የያኩትስክ ከተማ ፍርድ ቤት ፈቃድ ሰጠ። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ፖሊሶች የወንድም ኢጎርን ቤት ጨምሮ የስምንት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈተሹ። ወንድም ኢጎርና ሌሎች 21 የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ምርመራ ተደረገባቸው። አቃቤ ሕጉ ወንድም ኢጎር “የጽንፈኛ” ድርጅትን እንቅስቃሴ አስተባብሯል የሚል ክስ እንዲመሠረትበት ጠየቀ።

ለክሱ በቂ ማስረጃ ስላልተገኘ ኅዳር 20, 2019 ክሱ ወደ አቃቤ ሕግ ቢሮ ተመለሰ። አቃቤ ሕጉ ይግባኝ በመጠየቁ ክሱ ድጋሚ ወደ አውራጃ ፍርድ ቤት ተላከ። የካቲት 2020 መጀመሪያ ላይ ክሱ መታየት ጀመረ።

ወንድም ኢጎርና ባለቤቱ ናታሊያ ሁለት ሴት ልጆች አሏቸው። ውሳኔ የሚተላለፍበት ጊዜ ሲቃረብ ወንድም ኢጎርና ቤተሰቡ “በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት” መቋቋም እንዲችሉ እንጸልያለን።—ቆላስይስ 1:11