ጥቅምት 2, 2020
ሩሲያ
ሩሲያ ውስጥ አራት ወንድሞችና አንድ ባልና ሚስት እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ እስር ሊፈረድባቸው ይችላል
የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን
በዩልያኖቭስክ የሚገኘው የዛስቪያዥስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት በወንድም አሌክሳንደር ጃኒን፣ በወንድም ኸረን ኸቺክያን፣ በወንድም አንድሬ ታባኮቭ፣ በወንድም ሚካኼል ዘለንስኪ እንዲሁም በወንድም ሰርጌ ማይሲን እና በባለቤቱ በእህት ናታሊያ ላይ የቀረበውን ክስ ተመልክቶ ውሳኔውን ለማሳወቅ ጥቅምት 5, 2020 a ቀጠሮ ይዟል። ሁሉም ከሦስት እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ እስር ሊፈረድባቸው ይችላል። በተጨማሪም አቃቤ ሕጉ ገንዘባቸውና መኪኖቻቸው እንዲወረሱ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። አቃቤ ሕግ እንዲወረስ የጠየቀው ንብረት በድምሩ 1.57 ሚሊዮን ሩብል (20,000 የአሜሪካ ዶላር) ያህል ይገመታል።
አጭር መግለጫ
አሌክሳንደር ጃኒን
የትውልድ ዘመን፦ 1957 (አኸቢ፣ ሳካሊን ደሴት)
ግለ ታሪክ፦ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ 20 ዓመት አልፎታል። አሁን ጡረታ የወጣ ሲሆን አትክልት መንከባከብ ያስደስተዋል
ኸረን ኸቺክያን
የትውልድ ዘመን፦ 1985 (የረቫን፣ አርሜንያ)
ግለ ታሪክ፦ የኢኮኖሚክስ ዲግሪ አለው። በወጣትነቱ የነፃ ትግል ስፖርተኛ ነበር። ደግና ገራገር ሰው በመሆኑ ይታወቃል
አምላክን ይበልጥ ለማወቅና በሕግጋቱ ለመመራት ስለፈለገ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያታዊና እርስ በርሱ የሚስማማ መጽሐፍ መሆኑን ያደንቃል
ሰርጌ ማይሲን
የትውልድ ዘመን፦ 1965 (ኩሊባኪ፣ ኒዥኒ ኖቭጎሮድ)
ግለ ታሪክ፦ ከባለቤቱ ከናታሊያ ጋር የተዋወቀው የምሕንድስና ሙያ እያጠና በነበረበት ወቅት ነው። በ1991 ተጋቡ። ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ይሖዋን አብረው ያገለገሉ ሲሆን ራሳቸውን የቻሉ ሁለት ልጆች አሏቸው። ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ይወዳል፤ በተለይ ላክሮስ የተባለውን ስፖርት በጣም ይወደዋል
ናታሊያ ማይሲና
የትውልድ ዘመን፦ 1971 (ሌኒንግራድ፣ አሁን ሳንት ፒተርስበርግ ይባላል)
ግለ ታሪክ፦ ወላጆቿ ወታደሮች ነበሩ። በፋርማሲ ሙያ ከኮሌጅ እስከተመረቀችበት ጊዜ ድረስ የኖረችው ጀርመን ነው። ምግብ ማብሰልና ኬክ መጋገር ያስደስታታል
አንድሬ ታባኮቭ
የትውልድ ዘመን፦ 1973 (ሚንስክ፣ ቤላሩስ)
ግለ ታሪክ፦ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ነው። በ2006 ከማሪና ጋር ትዳር መሠረተ። ሁለቱም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው ተጠመቁ። የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን፣ በተለይ ደግሞ ሬዲዮና ኮምፒውተር መጠገን ያስደስተዋል
ሚካኼል ዘለንስኪ
የትውልድ ዘመን፦ 1960 (ቡሌስቲ፣ ሞልዶቫ)
ግለ ታሪክ፦ መርከበኛና የጭነት መኪና አሽከርካሪ ሆኖ ሠርቷል። በ1989 ከቪክቶሪያ ጋር ትዳር መሠረተ። በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እያደገ በመምጣቱ ተጠመቁ
የክሱ ሂደት
ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት የሩሲያ የፌዴራል ደህንነት ቢሮ በዩልያኖቭስክ የሚገኙ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ስልክ በመጥለፍ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች እነሱን መሰለል ጀመረ። የካቲት 24, 2019 የደህንነት ቢሮው በወንድም ሰርጌ ማይሲንና በባለቤቱ እንዲሁም በወንድም ኸረን ኸቺክያን፣ በወንድም አንድሬ ታባኮቭ እና በወንድም ሚካኼል ዘለንስኪ ላይ የወንጀል ምርመራ አስጀመረ።
ከሦስት ቀን በኋላ ማለዳ 11 ሰዓት ላይ ፖሊሶች የወንድም ኸረን ኸቺክያን፣ የወንድም አንድሬ ታባኮቭን እና የወንድም ሚካኼል ዘለንስኪን ቤት በረበሩ። ሦስቱም ወንድሞች ተይዘው ታሰሩ። በዚያው ዕለት ጠዋት እህት ናታሊያ ማይሲና ስልክ ተደወለላት። ደዋዩ መኪናዋ ጉዳት እንደደረሰበት ከነገራት በኋላ እሷና ባለቤቷ ሰርጌ ወደ ውጭ እንዲወጡ ነገራቸው። ወንድም ሰርጌ ማይሲን በሩን እንደከፈተ የፌዴራል ደህንነት አባላት ተንጋግተው ወደ ቤት ገቡ። ፖሊሶቹ ቤቱን ከፈተሹ በኋላ የቤተሰቡን የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ወሰዱ። ከዚያም ባልና ሚስቱ ታሰሩ።
በቀጣዩ ቀን በዩልያኖቭስክ የሚገኘው የዛስቪያዥስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ሰርጌ ማይሲን ያለፍርድ እንዲታሰር ወሰነ። እህት ናታሊያ ማይሲና እና ሌሎቹ ሦስት ወንድሞች ደግሞ በቁም እስር እንዲቆዩ ተደረገ።
ወንድም ሰርጌ ማይሲን 55 ቀን ያለፍርድ የታሰረ ከመሆኑም ሌላ 123 ቀን በቁም እስር ቆይቷል። እህት ናታሊያ ማይሲና፣ ወንድም ኸረን ኸቺክያን፣ ወንድም አንድሬ ታባኮቭ እና ወንድም ሚካኼል ዘለንስኪ ደግሞ ከ50 እስከ 55 ለሚሆኑ ቀናት በቁም እስር ቆይተዋል።
ግንቦት 15, 2019 ጠዋት ላይ የፌዴራል ደህንነት አባላት የወንድም አሌክሳንደር ጃኒንን ቤት ከፈተሹ በኋላ አሰሩት። ከዚያም ለሁለት ቀናት በማረፊያ ቤት ቆየ።
በአሁኑ ወቅት ስድስቱም አስፋፊዎች የተወሰነ ገደብ ተጥሎባቸዋል። በተጨማሪም ባለሥልጣናቱ በሌሎች መንገዶች ጫና እያሳደሩባቸው ነው። ለምሳሌ ወንድም ሰርጌ ማይሲንና ባለቤቱ እንዲሁም ወንድም አንድሬ ታባኮቭ የባንክ ሒሳባቸውን እንዳያንቀሳቅሱ ታግደዋል፤ በወንድም ሰርጌ ማይሲንና በባለቤቱ የባንክ ሒሳብ ውስጥ 500,000 ሩብል (6,313 ዶላር) ገደማ፣ በወንድም አንድሬ ታባኮቭ የባንክ ሒሳብ ውስጥ ደግሞ 600,000 ሩብል (7,575 ዶላር) ገደማ ይገኛል።
በሩሲያ የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚደርስባቸውን የእምነት ፈተና ተቋቁመው ሲጸኑ የሚከተለው ጥቅስ እንዲያበረታታቸው እንጸልያለን፦ “አምላክ መጠጊያችንና ብርታታችን፣ በጭንቅ ጊዜ ፈጥኖ የሚደርስልን ረዳታችን ነው።”—መዝሙር 46:1
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቀኑ ሊቀየር ይችላል