በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ እህት ናታሊያ ሶሮኪና እና እህት ማሪያ ትሮሺና

የካቲት 17, 2021
ሩሲያ

ሩሲያ ውስጥ አንድ ዓመት ያህል በማረፊያ ቤትና በቁም እስር ያሳለፉ ሁለት እህቶች ሊፈረድባቸው ይችላል

ሩሲያ ውስጥ አንድ ዓመት ያህል በማረፊያ ቤትና በቁም እስር ያሳለፉ ሁለት እህቶች ሊፈረድባቸው ይችላል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ይግባኛቸውን ውድቅ አደረገ

መስከረም 15, 2021 የስሞለንስክ ክልላዊ ፍርድ ቤት እህት ናታሊያ ሶሮኪና እና እህት ማሪያ ትሮሺና ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። መጀመሪያ ላይ የተላለፈባቸው ፍርድ በዚያው ይጸናል። በአሁኑ ወቅት ወህኒ አይወርዱም።

ሚያዝያ 22, 2021 በስሞለንስክ ክልል የሚገኘው የሲችዮቭስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት እህት ናታሊያ ሶሮኪና እና እህት ማሪያ ትሮሺና ጥፋተኛ ናቸው የሚል ፍርድ ያስተላለፈ ሲሆን የስድስት ዓመት የገደብ እስር በይኖባቸዋል።

አጭር መግለጫ

ናታሊያ ሶሮኪና

  • የትውልድ ዘመን፦ 1975 (ድሬዝደን፣ ጀርመን)

  • ግለ ታሪክ፦ ከጀርመን ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ሄደች፤ ከዚያም በስሞለንስክ ክልል ወደሚገኘው ወደ ሲችዮቭካ ተዛወረች። ነርስ ናት። የእጅ ሥራ ትወዳለች፤ እንዲሁም አገልግሎቷን ለማስፋት ስትል የተለያዩ ቋንቋዎችን መማር ያስደስታታል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጥንታለች። ስለ ፍጥረትና ስለ ወደፊቱ ተስፋ የተማረችው ነገር ልቧን ነካው። ይህም ለመንፈሳዊ ነገሮች ይበልጥ ትኩረት እንድትሰጥ አነሳሳት። ነሐሴ 1994 ተጠመቀች

ማሪያ ትሮሺና

  • የትውልድ ዘመን፦ 1977 (ሴንት ፒተርስበርግ)

  • ግለ ታሪክ፦ ከልጅነቷ ጀምሮ ስለ ታሪክ መማር ያስደስታታል። አስጎብኚ ሆና ሠርታለች። አገልግሎቷን ለማስፋት ስትል የሌላ አገር ቋንቋዎችን መማር ያስደስታታል

    ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጥንታለች። መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ እና ከሳይንስ አንጻር ትክክል መሆኑ በጣም አስደነቃት። ሕይወቷን ለይሖዋ ወስና ሐምሌ 1991 ተጠመቀች። እናቷም መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው ተጠምቀዋል፤ አሁን በሕይወት የሉም

የክሱ ሂደት

ጥቅምት 7, 2018 የፌዴራል ደህንነት አባላት እና የአካባቢው ፖሊሶች በሲችዮቭካ ከተማ የሚገኙ አራት ቤቶችን በረበሩ። የደህንነት አባላቱ የልጆችን ጨምሮ የ17 ወንድሞችና እህቶችን የግል ንብረት ወረሱ። እህት ናታሊያ ሶሮኪና እና እህት ማሪያ ትሮሺና ተይዘው ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ተደረጉ።

ማሪያ ቤቷ ስለተበረበረበት ጊዜ ስትናገር በእምነታቸው ምክንያት ስለታሰሩ የይሖዋ ምሥክሮች የሚናገሩ የሕይወት ታሪኮችን ማንበቧ ራሷን ለማዘጋጀት እንደጠቀማት ገልጻለች። እንዲህ ብላለች፦ “ቤቴ በተበረበረበት እና በቁጥጥር ሥር በዋልኩበት ወቅት ተረጋግቼ ነበር። እንዲህ ያለ ውስጣዊ መረጋጋት ይኖረኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው በአምላክ መንፈስ እርዳታ ብቻ ነው።”

ፍተሻው ከተካሄደ ከሁለት ቀናት በኋላ፣ በስሞለንስክ ከተማ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ሁለቱ እህቶቻችን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ከመታየቱ በፊት ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ወሰነ፤ በዚያም ለ191 ቀናት ቆይተዋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ በቁም እስር ከስድስት ወር በላይ አሳልፈዋል።

እነዚህ እህቶች ፈተናውን በጽናት መወጣት የቻሉት ከፈተናው በፊት ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ስለነበራቸው መሆኑን ገልጸዋል። ናታሊያ መንፈሳዊ አመለካከት መያዝ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልጻለች። ስደት ሲደርስብን የስደቱ ምንጭ ማን እንደሆነ መዘንጋት እንደሌለብን ተናግራለች። “ምንጊዜም ቢሆን በአምላክ ሕዝቦች ላይ ስደት የሚያመጣው ሰይጣን ነው፤ እያንዳንዳችን ለአምላክ ታማኝነታችንን ማሳየት ይኖርብናል” ብላለች።

ማሪያ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት በየቀኑ የሚጠናከር ነገር ነው፤ በመሆኑም የይሖዋን እርዳታና አሳቢነቱን በየዕለቱ በሕይወታችን ውስጥ ያየንባቸውን መንገዶች ማስተዋላችን በጣም አስፈላጊ ነው። በእያንዳንዱ ነገር በእሱ መታመንን ተማሩ። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ፍቅር አዳብሩ፤ የዘገባዎቹን ቅደም ተከተል ለማስታወስና የምትወዷቸውን ጥቅሶች በቃላችሁ ለመያዝ ጥረት አድርጉ።”

እህቶቻችን ‘በይሖዋ በመታመን እሱን ረዳታቸውና ጋሻቸው’ አድርገውታል፤ እነዚህ እህቶች ያሳዩት እምነትና ጽናት ለሁላችንም ግሩም ምሳሌ ነው!—መዝሙር 115:11