በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ዬካተሪና ፔጋሼቫ

ሚያዝያ 8, 2021
ሩሲያ

ሩሲያ ውስጥ እህት ዬካተሪና ፔጋሼቫ የወንጀል ክስ ቢመሠረትባትም በአቋሟ ጸንታለች

ሩሲያ ውስጥ እህት ዬካተሪና ፔጋሼቫ የወንጀል ክስ ቢመሠረትባትም በአቋሟ ጸንታለች

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት እህት ዬካተሪና ፔጋሼቫ የጠየቀችውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ

የማሪ ኤል ሪፑብሊክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ እህት ዬካተሪና ፔጋሼቫ የጠየቀችውን ይግባኝ ነሐሴ 4, 2021 ውድቅ አድርጓል። በመሆኑም ከዚህ ቀደም የተፈረደባት የስድስት ዓመት ተኩል የገደብ እስራት በዚያው ጸንቷል። እህት ዬካተሪና አሁን ወህኒ አትወርድም።

በማሪ ኤል ሪፑብሊክ የሚገኘው የጎርኖማሪስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ግንቦት 31, 2021 እህት ዬካተሪና ፔጋሼቫ ጥፋተኛ ናት የሚል ውሳኔ አሳልፏል። እህት ዬካተሪና የስድስት ዓመት ተኩል የገደብ እስራት ተፈርዶባታል። እርግጥ አሁን ወህኒ አትወርድም።

አጭር መግለጫ

ዬካተሪና ፔጋሼቫ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1989 (ጋኢንትሲ፣ ኪሮቭ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ለወላጆቿ ብቸኛ ልጅ ነች። መጻሕፍት ማንበብ፣ ግጥም መጻፍ እና መዘመር ትወዳለች። በጽዳት ሙያ ተሰማርታለች። አገልግሎቷን ለማስፋት ስትል የማሪ ቋንቋ ተምራለች

የክሱ ሂደት

ጥቅምት 3, 2019 እህት ዬካተሪና ፔጋሼቫ የማሪ ኤል ሪፑብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በዮሽካር ኦላ በቁጥጥር ሥር ዋለች። ፖሊሶች ቤቷን የፈተሹ ሲሆን የእህት ዬካተሪናን መጻሕፍት፣ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች፣ ደብዳቤዎችና ሰነዶች ወረሱ። እህታችን ከእምነት ባልንጀሮቿ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በመወያየቷ ምክንያት፣ እገዳ የተጣለበት ድርጅት በሚያካሂዳቸው እንቅስቃሴዎች በመካፈል ወንጀል ተከሰሰች።

ዬካተሪና እንዲህ ብላለች፦ “መንገድ ላይ ሳለሁ ፖሊሶች በድንገት መጡና እጄን ወደ ኋላ በመጠምዘዝ ከዛፍ ጋር አጣበቁኝ። ይሖዋ እንዲረዳኝ ልክ እንደ ነህምያ አጭር ጸሎት አቀረብኩ።” በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ ከ100 ቀናት በላይ በማረፊያ ቤት ቆይታለች። በአሁኑ ወቅት በቁም እስር ላይ ትገኛለች።

ዬካተሪና ማረፊያ ቤት በነበረችበት ወቅት በተደጋጋሚ ለጥያቄ ትጠራ ነበር። ያገኘችው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በዚህ ወቅት እንደጠቀማት ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት በተካፈልኩበት ወቅት ያገኘሁትን ሥልጠና እና የተሰጡኝን የቤት ሥራዎች አስታወስኩ። በተለይ የሚከተለው ሐሳብ በጣም አበረታቶኛል፦ በጠላቶቻችን ፊት ቀርበን ጥያቄዎቻቸውን በምንመልስበት ወቅት በጌታ ኢየሱስም ፊት ቆመናል። ይህን ማሰቤ ራሴን እንድቆጣጠርና ያላግባብ ለከሰሱኝ ባለሥልጣናት አክብሮት እንዳሳይ ረድቶኛል።”

ዬካተሪና በማረፊያ ቤትና በቁም እስር ከአንድ ዓመት በላይ በማሳለፏ የተለያዩ ችግሮች አጋጥመዋታል። ጤንነቷ ተጎድቷል፤ እንዲሁም ራሷን ለማስተዳደር መሥራት አልቻለችም። ከሁሉ የበለጠ የከበዳት ግን ከእናቷ እና ከአያቷ መለየቷ ነው። ዬካተሪና ይህ ሁሉ ፈተና ቢደርስባትም በታማኝነት ለመጽናት ቆርጣለች። እንዲህ ብላለች፦ “ጫና ባሳደሩብኝ መጠን እኔም መንፈሳዊ የጦር ትጥቄን አጠናክራለሁ። አሁን ምንም ነገር አልፈራም! በፊትም ደፋር ነበርኩ፤ አሁን ደግሞ በአምላክ መንፈስ እርዳታ ይበልጥ ደፋር ሆኛለሁ።”

ዬካተሪና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በምትጠባበቅበት ወቅት፣ አገልጋዮቹን በሙሉ በሚያበረታው በይሖዋ መታመኗን እንደምትቀጥል እርግጠኞች ነን።—ዘፀአት 15:2