ጥቅምት 8, 2020
ሩሲያ
ሩሲያ ውስጥ ወንድም አናቶሊ ቶካሬቭ የሦስት ዓመት ተኩል እስር ሊፈረድበት ይችላል
የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን
በኪሮቭ የሚገኘው የኦክታብርስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት በወንድም አናቶሊ ቶካሬቭ ላይ የተመሠረተውን ክስ ተመልክቶ ውሳኔውን ጥቅምት 23, 2020 a ለማሳወቅ ቀጠሮ ይዟል። ወንድም አናቶሊ ቶካሬቭ ሦስት ዓመት ተኩል ሊፈረድበት ይችላል።
አጭር መግለጫ
አናቶሊ ቶካሬቭ
የትውልድ ዘመን፦ 1958 (ባራኖቭስካያ፣ ኪሮቭ ክልል)
ግለ ታሪክ፦ ያሳደገችው እናቱ ነች። ጡረታ ከመውጣቱ በፊት የሶፍትዌር ኢንጂነር ሆኖ ይሠራ ነበር። ፎቶግራፍ ማንሳት እንዲሁም ቼዝና አኮርዲዮን መጫወት ያስደስተዋል። በ1979 ከማርጋሪታ ጋር ትዳር መሠረተ። ሁለት ልጆች አሏቸው
የሳይንስ እውቀቱ አምላክ የለሽ እንዲሆን አድርጎት ነበር። በ27 ዓመቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ፤ ከዚያም የክርስትና ትምህርት ከሳይንስ ጋር እንደማይጋጭ ተገነዘበ
የክሱ ሂደት
ግንቦት 24, 2019 ከፀረ ጽንፈኝነት ማዕከል የመጡ ፖሊሶች ወደ እነወንድም አናቶሊ ቶካሬቭ ቤት መጡ። ከዚያም ወንድም አናቶሊ ቶካሬቭን በጥያቄ ያፋጥጡት ጀመር። “በጽንፈኝነት” እንቅስቃሴ እንደሚካፈል ካላመነ በቤተሰቡ ላይ ክስ እንደሚመሠርቱ በመግለጽ አስፈራሩት። በኋላም ወንድም አናቶሊ ቶካሬቭ ለምርመራ ተወሰደ።
ከአምስት ወራት ገደማ በኋላ ወንድም አናቶሊ ቶካሬቭ በሩሲያ ፌዴሬሽን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ ባሉ ሁለት አንቀጾች ክስ ተመሠረተበት። “ጽንፈኛ” ድርጅትን በገንዘብ እንደሚደግፍ ተከሷል። በተጨማሪም አቃቤ ሕጉ ወንድም አናቶሊ ቶካሬቭ በቤቱ ውስጥ “ጽንፈኛ” ጽሑፍ የሚጠናበት ስብሰባ እንዳደራጀ ገልጿል፤ ይህን ያደረገው በነወንድም አናቶሊ ቶካሬቭ ቤት በድብቅ የተቀረጸ ኦዲዮ ቅጂን እንደ ማስረጃ በመጠቀም ነው።
ለወንድም አናቶሊ ቶካሬቭና ለቤተሰቡ እንጸልይላቸዋለን። ይሖዋ ምንጊዜም ‘ታማኝ እንደሚሆንላቸው’ እንተማመናለን።—መዝሙር 18:25
a ቀኑ ሊቀየር ይችላል