ነሐሴ 24, 2020
ሩሲያ
ሩሲያ ውስጥ ወንድም ካሳን ኮገት ከሚስቱና ከትንሽ ልጁ ተለይቶ ለሁለት ዓመት ሊታሰር ይችላል
የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን
ነሐሴ 31, 2020፣ a በኬሜሮቮ ግዛት የሚገኘው የቤሬዞቭስኪ ከተማ ፍርድ ቤት
አቃቤ ሕጉ የጠየቀው ፍርድ
የሁለት ዓመት እስር
አጭር መግለጫ
ካሳን ኮገት
የትውልድ ዘመን፦ 1983 (ሻህሪሳብዝ፣ ኡዝቤኪስታን)
ግለ ታሪክ፦ መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ፍላጎት ያደረበት በ1990ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ነው። በ2004 ወደ ሩሲያ ተዛውሮ መኖር የጀመረ ሲሆን የአገሪቱ ዜግነት ተሰጠው። በ2010 ዬካተሪና የተባለች ሴት አገባ። በ2012 ልጃቸው ቲሞፊ ተወለደ
የክሱ ሂደት
ሐምሌ 2018 ፖሊሶች የስምንት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ከፈተሹ በኋላ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻቸውን ወሰዱባቸው። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ወንድም ኮገት እና ባለቤቱ ወደ ፖሊስ ጣቢያው መጥተው የተወሰዱባቸውን ዕቃዎች እንዲቀበሉ ተነገራቸው። የካቲት 6, 2019 ፖሊስ ጣቢያው እንደደረሱ ፖሊሶች ወንድም ኮገትን አሰሩት። ወንድም ኮገት በሃይማኖታዊ አገልግሎት ስለተሳተፈ ብቻ ፖሊሶቹ በጽንፈኛ ድርጅት እንቅስቃሴ ውስጥ ተካፍሏል ብለው ከሰሱት።
ለሁለት ቀናት በፖሊስ ጣቢያው ከቆየ በኋላ ወደ ቤት ተመልሶ የቁም እስረኛ እንዲሆን ተደረገ። ነሐሴ 2019 ነፃ እስኪለቀቅ ድረስ ከ200 ለሚበልጡ ቀናት የቁም እስረኛ ሆኖ ቆይቷል። ከተለቀቀ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ክሱ በፍርድ ቤት መታየት ጀመረ።
ወንድም ኮገት እና ቤተሰቡ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እየተጠባበቁ ባሉበት በዚህ ሰዓት የሚያስጨንቃቸውን ነገር በይሖዋ ላይ መጣላቸውን እንደሚቀጥሉና እሱ እንደሚያስብላቸው በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እንደሚጽናኑ እንተማመናለን።—1 ጴጥሮስ 5:7
a ቀኑ ሊለወጥ ይችላል