መስከረም 23, 2020
ሩሲያ
ሩሲያ ውስጥ ወንድም ዩሪ ዛሊፓየቭ ሁለት ዓመት ሊፈረድበት ይችላል
የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን
በካባርዲኖ ባልካሪያን ሪፑብሊክ የሚገኘው የማይስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ጥቅምት 7, 2020 a ከወንድም ዩሪ ዛሊፓየቭ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል። ወንድም ዩሪ ዛሊፓየቭ ሁለት ዓመት ሊፈረድበት ይችላል።
አጭር መግለጫ
ዩሪ ዛሊፓየቭ
የትውልድ ዘመን፦ 1962 (ሳማራ)
ግለ ታሪክ፦ በብየዳ ሙያ እና በከባድ መኪና አሽከርካሪነት ተሰማርቶ የነበረ። ተራራ መውጣትና ግጥም ይወዳል
የልጅነት የትምህርት ቤት ጓደኛው ከሆነችው ከናታሊያ ጋር በ1983 ትዳር መሠረተ። ከአሥር ዓመት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን አብረው ማጥናት ጀመሩ። ሦስት ልጆች አሏቸው። ከጥቂት ዘመዶቻቸው ጋር ሆነው ሁሉም ይሖዋን ያመልካሉ
የክሱ ሂደት
ነሐሴ 20, 2016 ፖሊሶች በማይስኪ የሚገኝን አንድ የስብሰባ አዳራሽ ከወረሩ በኋላ “ጽንፈኛ” ተብለው የተፈረጁ አንዳንድ ጽሑፎቻችንን አዳራሹ ውስጥ አስቀመጡ። ወንድሞቻችን፣ ጽሑፎቹን ያስቀመጡት ፖሊሶቹ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ የቪዲዮ ማስረጃ ቢኖራቸውም ፍርድ ቤቱ ድርጅታችን 200,000 ሩብል (2,634 የአሜሪካ ዶላር) መቀጮ እንዲከፍል በየነ። ከዚህ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ከጥቂት ወራት በኋላ በወንድም ዛሊፓየቭ ላይ ክስ ተመሠረተበት።
አቃቤ ሕጉ፣ ወንድም ዛሊፓየቭ የታገዱ ጽሑፎችን እንዳሰራጨ እና አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች በሌላ ሃይማኖት አባላት ላይ የዓመፅ ድርጊት እንዲፈጽሙ እንዳነሳሳ ገልጿል። እነዚህ ክሶች “ሰዎች በጽንፈኛ እንቅስቃሴ እንዲካፈሉ ማነሳሳት” (የሩሲያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 280 ክፍል 1) በሚለው ሕግ ሥር የሚመደቡ ናቸው።
የክስ ሂደቱ የጀመረው ሰኔ 21, 2020 ነው። ክሱ ይሰማ በነበረበት ወቅት የአቃቤ ሕጉ ምሥክሮች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ አልፎ ተርፎም ክሱ ምንም መሠረት እንደሌለው የሚያሳዩ ሐሳቦች በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ወንድም ዛሊፓየቭ ሌሎችን ለዓመፅ እንዳነሳሳ የገለጹት አንዳንድ ምሥክሮች ወንድማችን ድርጊቱን ፈጸመ በተባለበት ጊዜ በቦታው እንኳ እንዳልነበሩ ታውቋል። በተጨማሪም የአቃቤ ሕጉ አንዳንድ ምሥክሮች በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ የተገኙትን የታገዱ ጽሑፎች ያስቀመጡት ፖሊሶች እንደሆኑ ገልጸዋል።
ወንድም ዛሊፓየቭ ፍርዱን እየተጠባበቀ ባለበት በዚህ ጊዜ እሱም ሆነ ቤተሰቡ ዳዊት ከተናገረው ከሚከተለው ሐሳብ መጽናኛ እንዲያገኙ እንጸልያለን፦ “ይሖዋ ብርታቴና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በእሱ ይተማመናል። ከእሱ እርዳታ ስላገኘሁ ልቤ ሐሴት ያደርጋል።”—መዝሙር 28:7
a ቀኑ ሊቀየር ይችላል