ሰኔ 5, 2020
ሩሲያ
ሩሲያ ውስጥ ወንድም ጀናዲ ሽፓኮቭስኪ የሰባት ዓመት ተኩል እስር ሊፈረድበት ይችላል
የፓስኮቭ ከተማ ፍርድ ቤት፣ በ61 ዓመቱ በወንድም ጀናዲ ሽፓኮቭስኪ ላይ የተመሠረተውን ክስ ተመልክቶ ሰኔ 8, 2020 ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል። ወንድም ጀናዲ ሽፓኮቭስኪ “ጽንፈኛ ነው” ተብሎ የተከሰሰው ቤቱ ውስጥ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዲደረጉ ስለፈቀደ ነው። አቃቤ ሕጉ በወንድም ጀናዲ ሽፓኮቭስኪ ላይ የሰባት ዓመት ተኩል እስር እንዲፈረድበት ጠይቋል።
በ2018 መጀመሪያ ላይ የፌዴራል ደህንነት ፖሊሶች የወንድም ጀናዲ ሽፓኮቭስኪን ቤት መሰለል የጀመሩ ሲሆን ለበርካታ ወራት ቤተሰቡን ሲከታተሉ ቆይተዋል። ሰኔ 3, 2018 ከቀኑ 6:45 ላይ ፖሊሶቹ ከታጠቁ ወታደሮች ጋር በመሆን የወንድም ጀናዲ ሽፓኮቭስኪን በር በርግደው በመግባት ለስድስት ሰዓት ያህል ቤቱን በረበሩ፤ በወቅቱ የተወሰኑ ሰዎች ሰላማዊ ስብሰባ እያደረጉ ነበር።
ፖሊሶቹ የይሖዋ ምሥክሮቹን ታብሌቶችና ስልኮች ከወረሱ በኋላ ወንድሞቻችንን ለምርመራ ወሰዷቸው። መርማሪዎቹ ወንድሞቻችንን የሰደቧቸው ከመሆኑም ሌላ ከሥራ እንደሚባረሩና እንደሚታሰሩ በመግለጽ አስፈራርተዋቸዋል። የወንድም ጀናዲ ሽፓኮቭስኪ ምርመራ እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ ቀጥሎ ነበር።
መጋቢት 19, 2019 ወንድም ጀናዲ ሽፓኮቭስኪ “የጽንፈኛ” ድርጅትን እንቅስቃሴ በማደራጀት ወንጀል ተከሰሰ። ከአምስት ወራት በኋላ ደግሞ “የጽንፈኛ ድርጅትን እንቅስቃሴ በገንዘብ ደግፏል” በሚል ተጨማሪ ክስ ተመሠረተበት።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እየተቃረበ ሲመጣ ይሖዋ የወንድም ጀናዲ ሽፓኮቭስኪ ቤተሰብ ጠንካራ እንዲሆኑ እንደሚረዳቸው በመተማመን ወደ እሱ እንጸልያለን፤ የታማኝነታቸውንና የጽናታቸውን ዋጋ እንደሚያገኙ እርግጠኞች ነን።—2 ዜና መዋዕል 15:7