በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ እህት ዩሊያ ሚረትስካያ፣ እህት ኤልቪራ ግሪዳሶቫ፣ እህት ዬቭጌኒያ ላጉኖቫ፣ እህት ታትያና ቡደንቹክ እና እህት ናዴዥዳ ጀርመን የካቲት 2020 በኦረንበርግ ከሚገኘው እስር ቤት ውጭ ቆመው

ሰኔ 23, 2021
ሩሲያ

ሩሲያ ውስጥ የታሰሩት ወንድሞች ሚስቶች ያጋጠማቸውን ፈተና በይሖዋ በመታመን እየተቋቋሙ ነው

ሩሲያ ውስጥ የታሰሩት ወንድሞች ሚስቶች ያጋጠማቸውን ፈተና በይሖዋ በመታመን እየተቋቋሙ ነው

በሩሲያ በእምነታቸው ምክንያት ከታሰሩት ወንድሞቻችን ብዙዎቹ ባለትዳርና የልጆች አባት ናቸው፤ በመሆኑም የእነሱ መታሰር የሚጎዳው እነሱን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውንም ጭምር ነው። ሚስቶቹ ከትዳር ጓደኛቸው፣ ልጆቹ ደግሞ ከአባታቸው መለየታቸው በራሱ ያስከተለባቸው ጭንቀት ሳያንስ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችም አጋጥመዋቸዋል። ባሎቻቸው የታሰሩባቸው አሥር እህቶች ስሜታቸውን በግልጽ የሚያሳይ ደብዳቤ ለሩሲያ ባለሥልጣናት ጽፈዋል። ደብዳቤው እንዲህ ይላል፦ “ይህን ክፍት ደብዳቤ የላክንላችሁ ጭንቀታችንን እንድትረዱልን ለመማጸን ነው። የምንወዳቸው ሰዎች . . . ከእኛ፣ ከልጆቻችን እና ከወዳጆቻቸው ጋር ሆነው የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በማንበባቸውና ለአምላክ በመጸለያቸው ብቻ ወህኒ ተጥለዋል።”

ከእነዚህ ውድ እህቶቻችን አንዳንዶቹ፣ ምን ዓይነት ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟቸው እንዲሁም ባሎቻቸው እስር ቤት ባሉበት ወቅት ይሖዋ እንዴት እንደረዳቸው ተናግረዋል።

መገናኘትና ጥየቃ

ብዙዎቹ እህቶች በቴክኒክ ችግር ምክንያት ከባሎቻቸው ጋር በስልክ መነጋገር አይችሉም። ከዚህም ሌላ ወደ እስር ቤት የሚልኳቸው ደብዳቤዎች ለባሎቻቸው የሚደርሷቸው በጣም ዘግይተው ነው፤ አንዳንዴም ጨርሶ ላይደርሱ ይችላሉ።

ለምሳሌ የእህት ዬቭጌኒያ ላጉኖቫ ባለቤት የሆነው ፊሊክስ ማክሃማዲየቭ ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ቆይቷል። ዬቭጌኒያ ረዘም ላለ ጊዜ ወሬውን ሳትሰማ የምትቆይባቸው ጊዜያት ነበሩ። ‘ጤንነቱ እንዴት ይሆን? የምልክለት ደብዳቤ ሳይደርሰው ቀርቶ እንደተረሳ ይሰማው ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ በጣም ያስጨንቃት እንደነበር ተናግራለች።

ብዙዎቹ ሚስቶች ባሎቻቸውን ለመጠየቅ ረጅም መንገድ መጓዝ አስፈልጓቸዋል። (“እህቶቻችን ባሎቻቸውን ለመጠየቅ መጓዝ የሚጠበቅባቸው ርቀት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ለምሳሌ ዬቭጌኒያ “ባለቤቴን እስር ቤት ሄጄ ለመጠየቅ በመኪና ከ800 ኪሎ ሜትር በላይ እጓዝ ነበር” ብላለች። ባለቤቷን ጠይቃ ወደ ቤቷ ለመመለስ በአማካይ ከሦስት እስከ አራት ቀን ይወስድባታል። እስከ 1,000 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት የሚጓዙ እህቶችም አሉ። እነዚህ እህቶች እስር ቤት ከደረሱ በኋላም ብዙውን ጊዜ ውጭ ተሰልፈው ለረጅም ሰዓት መጠበቅ አለባቸው።

የእህት አይሪና ክሪስተንሰን ባለቤት የሆነው ዴኒስ ከ2017ቱ እገዳ በኋላ የታሰረ የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክር ነው። አይሪና በኦርዮል ከሚገኘው ቤቷ ተነስታ በልጎቭ በሚገኝ እስር ቤት ያለውን ባለቤቷን ለመጠየቅ በየጊዜው 200 ኪሎ ሜትር ትጓዛለች። እንዲህ ብላለች፦ “ወደ እስር ቤቱ መሄድ አካላዊና ስሜታዊ ጫና ይፈጥራል። ጠዋት 2:00 እስር ቤቱ ደርሼ አስፈላጊውን ሰነድ ማስገባት እንድችል ሌሊት 9:30 ከቤቴ መውጣት አለብኝ። ጥየቃ የሚጀመረው 5:00 ስለሆነ እስከዚያ ድረስ መኪናዬ ውስጥ ቁጭ ብዬ እጠብቃለሁ።” አይሪና ሁኔታውን ለመቋቋም የረዳት ምን እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ እንዲረዳኝ ብዙ ጊዜ እጸልያለሁ፤ በተጨማሪም በአቅራቢያዬ ያሉትን፣ ወህኒ ቤት የወረዱትንና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቼን እንዲደግፋቸው እለምነዋለሁ።”

ብቸኝነት

እህት ናዴዥዳ ጀርመን ከባለቤቷ ከጀናዲ ከተለየች ከሁለት ዓመት በላይ ሆኗታል። ባሎቻቸው እንደታሰሩባቸው ሌሎች እህቶች ሁሉ ናዴዥዳም ከባለቤቷ መለየቷ የፈጠረባትን የብቸኝነት ስሜት መቋቋም አስፈልጓታል። ሆኖም ናዴዥዳ እንዲህ ብላለች፦ “ጉባኤው ከቀድሞው ይበልጥ እንደ ቤተሰቤ ሆኖልኛል። እኔንም ሆነ ባለቤቴን ከልባቸው እንደሚወዱንና እንደሚያስቡልን በግልጽ ተመልክቻለሁ።”

የእህት ዩሊያ ሚረትስካያ ባለቤት የሆነው አሌክሲ ከጀናዲ ጋር ታስሯል፤ ዩሊያ እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞችና እህቶች በቤት ውስጥ ሥራዎች ያግዙኛል። በሚያስፈልገኝ ጊዜ ሁሉ እንደሚደርሱልኝ የምተማመንባቸው ወዳጆች እንዳሉኝ ማወቄ አጽናንቶኛል።”

ልጆች ማሳደግ

እህት ታትያና ቡደንቹክ ባለቤቷ አሌክሲ መስከረም 2019 ከታሰረ ወዲህ ሁለት ልጆቻቸውን ብቻዋን ለማሳደግ ተገድዳለች። እንዲህ ብላለች፦ “ልጆቻችን ባሉን በረከቶች፣ ይሖዋ በሰጠን ነገሮች እንዲሁም ሁልጊዜ በሚያደርግልን ድጋፍ ላይ ለማተኮር ጥረት ያደርጋሉ። ይህ መከራ ጊዜያዊ እንደሆነ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በይሖዋ መታመንና ለእሱ ታማኝ መሆን እንዳለብን ያውቃሉ።”

የእህት ናታሊያ ፊላቶቫ ባለቤት የሆነው ሰርጌ ፊላቶቭ መጋቢት 2020 የስድስት ዓመት እስራት ተፈርዶበታል፤ በመሆኑም ናታሊያ አራት ልጆቻቸውን የምታሳድገው ብቻዋን ነው። ልጆቹን በተመለከተ እንዲህ ብላለች፦ “አባታቸውን እንደሚናፍቁ እና ስለ ደህንነቱ እንደሚጨነቁ አስተውላለሁ። በጸሎታቸው ላይ ስለ እሱ ይጠቅሳሉ። ትንሿ ልጃችን ለአባቷ ደብዳቤ ስትጽፍለት ‘እኛ ደህና ነን፤ ስለ እኛ አታስብ’ ትለዋለች። እርግጥ ነው፣ ከቤተሰቡ ጋር የሚቀላቀልበትን ጊዜ እንደምንናፍቅ የታወቀ ነው።”

ናታሊያ እና ልጆቿ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመከተል አኗኗራቸውን ቀላል ለማድረግ ይጥራሉ። ናታሊያ እንዲህ ብላለች፦ “በትንሽ ገንዘብ መኖርንና ቆጣቢ መሆንን ተምረናል። ወጪዎቻችንን ለመሸፈንና ሌሎች የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለመግዛት የሚበቃ ገንዘብ አለን።”

መንፈሳዊ አመለካከት መያዝ

እህቶቻችን እንዲህ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም አዘውትረው በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በመካፈል መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀዋል። ዩሊያ እንዲህ ብላለች፦ “የሚደርሱንን ጽሑፎች በሙሉ ለማንበብ እጥራለሁ። እንዲያውም ለሁለት ሰው ነው የማጠናው ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም ከአሌክሲ ጋር ስንገናኝ ካጠናሁት ውስጥ ዋና ዋናውን ነጥብ አስታውሼ ለእሱ ለማካፈል ጥረት አደርጋለሁ።” ናዴዥዳ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “በይሖዋ እርዳታ ማንኛውንም ችግር መፍታት ይቻላል! ከይሖዋ ጋር በጣም የጠበቀ ወዳጅነት አለኝ። ኃያል በሆነው አባቷ እቅፍ ውስጥ እንዳለች ትንሽ ልጅ እንደሆንኩ ይሰማኛል! በተጨማሪም ሌሎችን ስረዳ እኔም እበረታታለሁ።”

ናታሊያም እንዲህ ብላለች፦ “አንዲት እህት እንዲህ ብላ ነበር፦ ‘ከአምላክ ሕዝቦች መካከል ማጽናኛ የማያስፈልገው የለም፤ ከአምላክ ሕዝቦች መካከል ሌሎችን ማጽናናት የማይችልም የለም።’ እኔም ሌሎችን ሳጽናና እና ሳበረታታ እርካታ አገኛለሁ።” ናታሊያ አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ከባለቤቴ መለየቴ በስሜታዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ ከባድ ቢሆንብኝም ለራሴ ላለማዘን ወይም በተስፋ መቁረጥ ስሜት ላለመዋጥ ጥረት አደርጋለሁ። ሰይጣን ተስፋ እንዲያስቆርጠኝ ፈጽሞ አልፈቅድም!”

በሩሲያም ሆነ በሌሎች አገራት የሚገኙ የቤተሰባቸው አባል የታሰረባቸው ክርስቲያኖች የሚያሳዩትን ጽናት ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር በእጅጉ ያደንቃል። ይሖዋ ‘በዓይኑ ፊት ውድ የሆኑትን’ እነዚህን ክርስቲያኖች ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው እንተማመናለን።—ኢሳይያስ 43:4ሀ