በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ቡድን እንደገለጸው የሚከተሉት አሥር ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ሌሎች ስምንት የይሖዋ ምሥክሮች ሩሲያ ውስጥ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በፖሊስ ተይዘዋል እንዲሁም ታስረዋል፤ አንድሬ ማግሊቭ፣ ኢጎር ኤጎዛርያን፣ ሩስላን ኮራልዮቭ፣ ቭላዲሚር ኩልያሶቭ እና ቫለሪ ሮጎዝን፣ (የመጀመሪያው መደዳ፣ ከግራ ወደ ቀኝ)፤ ቫለሪ ሻሌቭ፣ ታትያና ሻምሼቫ፣ ኦልጋ ሲላዬቫ፣ አሌክሳንደር ሶሎቭየቭ እና ዴኒስ ቲሞሺን (ሁለተኛው መደዳ፣ ከግራ ወደ ቀኝ)

ግንቦት 18, 2020
ሩሲያ

ሩሲያ 18 የይሖዋ ምሥክሮችን ማሰሯ ዓለም አቀፉን ሕግ እንደሚያስጥሳት የተ.መ.ድ. ባለሙያዎች ገለጹ

ሩሲያ 18 የይሖዋ ምሥክሮችን ማሰሯ ዓለም አቀፉን ሕግ እንደሚያስጥሳት የተ.መ.ድ. ባለሙያዎች ገለጹ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ቡድን ባለ 15 ገጽ ሰነድ አውጥቶ ነበር፤ ሰነዱ፣ ሩሲያ ከግንቦት 2018 እስከ ሐምሌ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ከተሞች ያሉ 18 የይሖዋ ምሥክሮችን ማሰሯ ዓለም አቀፉን ሕግ እንደሚያስጥሳት ይገልጻል። ይህ የባለሙያዎች ቡድን፣ በእስራት ላይ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በአስቸኳይና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጥያቄ አቅርቧል።

የሰነዱ የመጀመሪያ ቅጂ የወጣው ግንቦት 15, 2020 ነበር። የሰነዱ የመጨረሻ ቅጂ ደግሞ በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረ ገጽ ላይ ይወጣል።

አግባብ ያልሆነ እስራት አጣሪ ቡድን ተብሎ የሚጠራው ይህ የባለሙያዎች ቡድን የእምነት ባልንጀሮቻችንን የሚደግፍ ውሳኔ ሲያስተላልፍ በአንድ ዓመት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። አጣሪ ቡድኑ፣ አሁን ባወጣው ሰነድ ላይ የሩሲያ መንግሥት በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ላይ የፈጸማቸውን ፍትሕ የጎደላቸው ድርጊቶች አውግዟል።

ባለሥልጣናቱ የይሖዋ ምሥክሮቹን ሲያስሩ “ከልክ ያለፈ ኃይል” መጠቀማቸውን ቡድኑ ገልጿል፤ ሰነዱ ይህን በተመለከተ “የፖሊስ ኃይል እንዲህ ያለ እርምጃ እንዲወስድ የሚያበቃ ምንም ምክንያት የለውም” ብሏል፤ በተጨማሪም “የትኛውም [የይሖዋ ምሥክር] በፖሊስ መያዝም ሆነ ያለፍርድ በእስር መቆየት አልነበረበትም፤ እንዲሁም አንዳቸውም ቢሆኑ ችሎት ፊት መቅረብ አልነበረባቸውም፤ ወደፊትም ቢሆን ሊቀርቡ አይገባም” ብሏል።

ቡድኑ፣ የይሖዋ ምሥክሮቹ ጽንፈኝነት በሚንጸባረቅባቸው እንቅስቃሴዎች ተሳትፈዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎታል። ወንድሞችና እህቶች “የሃይማኖት ነጻነት መብታቸውን ከመጠቀም” ውጭ ምንም ነገር እንዳላደረጉ አብራርቷል።

ቡድኑ ባሰፈረው መግለጫ ላይ ችሎቱ የወንድሞችን ክስ ለማየት የተጠቀመባቸውን ዘዴዎች አውግዟል። ለምሳሌ ያለፍርድ እስር ላይ የነበሩ ሁለት እህቶች ችሎት ፊት በቀረቡበት ወቅት የተቀመጡት በብረት በታጠረ ክፍል ውስጥ ነበር። አጣሪ ቡድኑ እንዳብራራው በዓለም አቀፉ ሕግ መሠረት ማንኛውም ሰው “በሕግ ፊት ቀርቦ ጥፋተኝነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ እንደ ንጹሕ ሰው የመቆጠር መብት” አለው። በዚህም ምክንያት እህቶቻችን “አደገኛ ወንጀለኞች በሚያዙበት መንገድ ሊያዙ አይገባም፤ ለምሳሌ በካቴና መታሰር ወይም በችሎቱ ወቅት በብረት በታጠረ ክፍል ውስጥ መቀመጥ” አልነበረባቸውም።

የሩሲያ መንግሥት 18ቱን የይሖዋ ምሥክሮች ከቀረበባቸው የወንጀል ክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲያደርጋቸው እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ሕግ ጋር በሚስማማ መልኩ ማካካሻ እንዲሰጣቸው አጣሪ ቡድኑ ጠይቋል። በተጨማሪም መንግሥት፣ የይሖዋ ምሥክሮቹ እንዲህ ያለ ኢፍትሐዊ ድርጊት እንዲፈጸምባቸው ባደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ “የተሟላና ገለልተኛ የሆነ ምርመራ እንዲያደርግ” እንዲሁም “[የይሖዋ ምሥክሮቹን] መብት በጣሱት አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ” ተጠይቋል።

ሰነዱ እንደሚገልጸው ሩሲያ ውስጥ ከእነዚህ 18 የይሖዋ ምሥክሮች በተጨማሪ “የሃይማኖት ነጻነት መብታቸውን በመጠቀማቸው ብቻ በፖሊስ የሚያዙ፣ የሚታሰሩና የወንጀል ክስ የሚመሠረትባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው”፤ ይህ ደግሞ የሃይማኖት ነጻነት እንዲከበር የሚደነግገውንና ሩሲያ አባል የሆነችበትን ዓለም አቀፍ ስምምነት የሚጥስ ነው። በመሆኑም ይህ ሰነድ ያተኮረው ስማቸው በተጠቀሰ 18 የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ቢሆንም አጣሪ ቡድኑ በግልጽ እንዳሰፈረው በሰነዱ ላይ የሚገኘው ሐሳብ “ለሌሎች ተመሳሳይ ሁኔታዎችም ይሠራል።”

አጣሪ ቡድኑ ለሩሲያ መንግሥት ያቀረበው ጥያቄ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ነጻ እንዲለቀቁ ያደርጋል ብለን በእርግጠኝነት መጠበቅ አንችልም፤ ይሁንና ሁኔታቸውን ሊያሻሽለው እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን። የሩሲያ መንግሥት የሚሰጠውን ምላሽ እንጠብቃለን። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሩሲያ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚደርስባቸውን ስደት በድፍረት እየተጋፈጡ ነው፤ አፍቃሪ አባታችን የሆነው ይሖዋም በእሱ በመታመናቸው ደስታና ሰላም እንደሚሰጣቸው እንተማመናለን።—ሮም 15:13