በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ቪክቶር ባቹሪን፣ ወንድም አሌክሳንደር ኮስትሮቭ እና ወንድም አርተር ኔትሬባ

ሚያዝያ 27, 2021
ሩሲያ

በሊፔትስክ የሚኖሩ ሦስት ወንድሞች በእምነታቸው ምክንያት ለ331 ቀናት ማረፊያ ቤት ከቆዩ በኋላ ለፍርድ ሊቀርቡ ነው

በሊፔትስክ የሚኖሩ ሦስት ወንድሞች በእምነታቸው ምክንያት ለ331 ቀናት ማረፊያ ቤት ከቆዩ በኋላ ለፍርድ ሊቀርቡ ነው

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ይግባኛቸውን ውድቅ አደረገ

ጥር 20, 2022 የሊፔትስክ ክልላዊ ፍርድ ቤት ወንድም ቪክቶር ባቹሪን፣ ወንድም አሌክሳንደር ኮስትሮቭ እና ወንድም አርተር ኔትሬባ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። በመሆኑም የተጣለባቸውን የገንዘብ መቀጮ መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

ኅዳር 24, 2021 በሊፔትስክ የሚገኘው የሶቬትስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ቪክቶር፣ አሌክሳንደር እና አርተር ጥፋተኛ ናቸው በማለት እያንዳንዳቸው 500,000 ሩብል (6,700 የአሜሪካ ዶላር) መቀጮ እንዲከፍሉ ወስኗል። ሆኖም አሁን መክፈል የሚጠበቅባቸው 300,000 ሩብል (4,000 የአሜሪካ ዶላር) ነው፤ ምክንያቱም ማረፊያ ቤት የቆዩበት ጊዜ ግምት ውስጥ ይገባል። አሁን ወኅኒ አይወርዱም።

አጭር መግለጫ

ቪክቶር ባቹሪን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1962 (ፓቭሎቭስኪ ፖሳድ፣ ሞስኮ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን አንዲት የልጅ ልጅ አለችው። በ1990ዎቹ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ከዚያም በ1992 ተጠመቀ። በአሁኑ ጊዜ ከቤተሰቡ መካከል የይሖዋ ምሥክር የሆነው እሱ ብቻ ነው

አሌክሳንደር ኮስትሮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1961 (ሶርታቫላ፣ የካሬሊያ ሪፑብሊክ)

  • ግለ ታሪክ፦ የአውሮፕላን አብራሪ፣ የጋዝ እና የኤሌክትሪክ በያጅ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ባለሙያ ሆኖ ሠርቷል። በ1997 ከባለቤቱ ከላሪሳ ጋር ትዳር መሠረተ። ሁለት ልጆች አሏቸው። አሁን ጡረታ የወጣ ሲሆን ዓሣ ማጥመድ ያስደስተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረግ ያለውን ጥቅም ከተገነዘበ በኋላ በ2002 ተጠመቀ

አርተር ኔትሬባ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1978 (ግሎዴኒ፣ ሞልዶቫ)

  • ግለ ታሪክ፦ በ1995 ስቬትላናን አገባ። እሱና ባለቤቱ አንዲት ሴት ልጅ ወልደዋል። ቤተሰቡ ሥራ ለመፈለግ ወደ ሊፔትስክ ተዛውረው መኖር ጀመሩ። አሁን የሽያጭ ኃላፊ ሆኖ ይሠራል። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ፣ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት እንደሚረዳ ተገነዘበ። በመሆኑም በ2000 ተጠመቀ

የክሱ ሂደት

ታኅሣሥ 2, 2019 የሊፔትስክ ክልል ፖሊሶች በሰባት ቤቶች ላይ ፍተሻ አካሄዱ። ወንድም ቪክቶር ባቹሪን፣ ወንድም አሌክሳንደር ኮስትሮቭ እና ወንድም አርተር ኔትሬባ ታሰሩ። የፌዴራል ደህንነት አገልግሎት፣ ወንድሞች “በሕገ መንግሥቱ ሥርዓት ላይ ከባድ ወንጀል” እንደፈጸሙ በመግለጽ ክስ መሠረተባቸው፤ ይህ ክስ የተመሠረተባቸው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘታቸውና በሌሎች የአምልኮ እንቅስቃሴዎች በመካፈላቸው ነው። ወንድሞች ለ331 ቀናት ያህል በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ተደርገዋል።

አሌክሳንደር በማረፊያ ቤት በቆየባቸው ጊዜያት ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና እንደተጠናከረ አስተውሏል፤ “እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ሲያጋጥሟችሁ ዋነኛው የብርታታችሁ ምንጭ ይሖዋና እሱ የሚሰጠው ድጋፍ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ” ብሏል።

አርተር ቁርጥ ውሳኔው ምን እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ደስታዬን እና አዎንታዊ አመለካከቴን ይዤ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ። ይህ ሁሉ ነገር ጊዜያዊ እንደሆነና አባቴ [ይሖዋ] ቁስሌን እንደሚፈውስልኝ ለማስታወስ እሞክራለሁ። በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ስለ ቅዱሱ አምላካችን ይሖዋ የምናገርበት አጋጣሚ አላጣም።”

ቪክቶር እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ እነዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች ባጋጠሙኝ ወቅት እውነተኛ ጓደኛዬ እንደሆነ አሳይቶኛል። እሱ የቅርብ ወዳጄ እንደሆነ የማይበት ብዙ አጋጣሚ አግኝቻለሁ።”

ቪክቶር እስር ላይ በነበረበት ወቅት፣ ወንድሞችና እህቶች የይሖዋ ምሥክር ላልሆነችው ባለቤቱ ድጋፍ አድርገውላታል። ቪክቶር የተሰማውን ከፍተኛ አድናቆት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ እህቶች አሳቢነት ስላሳዩአት በጣም ተደስታለች። ቤተሰቦቼ በዚህ አጋጣሚ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለውን ፍቅር ማስተዋል እንደቻሉ እርግጠኛ ነኝ።”

ይሖዋ በሩሲያም ሆነ በሌሎች አገሮች ስደት እየደረሰባቸው ያሉ ወንድሞቻችንን ማጽናናቱን እንደሚቀጥል እንተማመናለን።—ኢሳይያስ 51:12